የሌሶቶ ብሔራዊ ቡድን አዲስ አበባ ገብቷል

በነገው ዕለት ከዋልያው ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሚያደርገው የሌሶቶ ብሔራዊ ቡድን ከደቂቃዎች በፊት አዲስ አበባ ደርሷል።

የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከቀናት በኋላ እንደሚጀምሩ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከማላዊ እና ግብፅ ጋር ላሉበት ጨዋታዎች ዝግጅቱን ከትናንት በስትያ የጀመረ ሲሆን ከፍልሚያቹ በፊት ያለበትን አሁናዊ አቋም ለማወቅ ነገ እና ሰኞ ከሌሶቶ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል።

ሲሸልስን በመርታት ለአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣሪያ የበቃችው ሌሶቶ ለኮሞሮስ እና ኮትዲቯር ጨዋታ ሦስት ግብ ጠባቂ፣ አስራ አንድ ተከላካይ፣ ስምንት አማካይ እና ሦስት አጥቂዎችን በመያዝ ከቀናት በፊት ዝግጅት ጀምራ የነበረ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም ደቡብ አፍሪካ ላይ ከናሚቢያ አቻዋ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርጋ ነበር። ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ ሁለተኛ እና ሦስተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎቹን ከኢትዮጵያ ጋር ለማድረግ አዲስ አበባ ቦሌ ዐየር ማረፊያ ደርሰዋል። ልዑካን ቡድኑም ካሳንቺስ በሚገኘው ጁፒተር ሆቴል ማረፊያውን እንደሚያደርግ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ ዛሬን ጨምሮ ሦስት ተከታታይ ቀናት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ልምምዱን ሲያከናውን ቆይቷል። በክለብ ቆይታቸው መጠነኛ ጉዳት አስተናግደው የነበሩት አቡበከር ናስር፣ ያሬድ ባየህ እና ሱራፌል ዳኛቸው ከህክምና ባለሙያዎች እና የአካል ብቃት ባለሙያው ጋር በመሆን በቶሎ እንዲያገግሙ የሚያደርጋቸውን ሥራ ሲከውኑ እንደነበር አስተውለናል። በተለይ አቡበከር እና ሱራፌል የማሟሟቅ እና የማፍታታት ስራዎችን ከአጋሮቻቸው ጋር ከሰሩ በኋላ ተነጥለው ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሲከውኑ ከርመዋል። ይህ የሚደረገው ተጫዋቾቹን ከከፋ ጉዳት ለመጠበቅ ታስቦ እንደሆነ እንጂ ከጨዋታዎች የሚያርቃቸው ሁኔታ ላይ ተገኝተው እንዳልሆነ ሰምተናል።

የኢትዮጵያ እና ሌሶቶ ጨዋታ ነገ 10 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሲደረግ በኢትዮጵያዊያን ዋና እና ረዳት ዳኞች እንደሚመራ ታውቋል። ቡድኖቹ አዳራቸውን እዚሁ መዲናችን አድርገው ቀትር 7 ሰዓት ወደ ስፍራው እንደሚጓዙ ተጠቁሟል።