አዳማ ላይ በአቋም መፈተሻ ጨዋታ የተገናኙት የኢትዮጵያ እና ሌሶቶ ብሔራዊ ቡድኖች 1-1 ወጥተዋል።
ከፊታቸው ወሳኝ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የሚጠብቋቸው ዋልያዎቹ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ከሌሶቶ አቻቸው ጋር ለማድረግ ካሰቧቸው ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ውስጥ ቀዳሚውን ዛሬ አከናውነዋል።
በመጀመሪያው የብሔራዊ ቡድኑ አሰላለፍ ውስጥ በአመዛኙ ነባር የሆነው ስብስብ ጥቅም ላይ ሲውል ፋሲል ገብረሚካኤል በግብ ጠባቂነት አስራት ቱንጆ ፣ ምኞት ደበበ ፣ ያሬድ ባየህ እና ረመዳን የሱፍ በተከላካይ መስመር መስዑድ መሀመድ ፣ ጋቶች ፓኖም እና ሱራፌል ዳኛቸው አማካይ ክፍል ላይ እንዲሁም ዳዋ ሆቴሳ ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና በረከት ደስታ ደግሞ በአጥቂነት ተሰልፈዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የቡድኑ እንቅስቃሴ በአመዛኙ ወደራሳቸው የሜዳ ክልል የሸሹት ሌሶቶዎችን ለማስከፈት በመሞከር ላይ ያመዘነ ነበር። ሆኖም 20ኛው ደቂቃ ላይ እንግዶቹ ከመሀል ሜዳ ያሻሙት የቅጣት ምት ኳስ በኢትዮጵያዊያኑ በአግባቡ መራቅ ሳይችል ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ የተላከውን ኳስ ማክሀ ቱሜሎ ሮጦ ወደ ሳጥን በመግባት ራሱን ነፃ አድርጎ ጎል አድርጎያል።
ከግቡ በኋላ ዋልያዎቹ በቅብብሎች ተጋጣሚያቸውን አስከፍተው ሰብረው ለመግባት ብዙ ቢጥሩም ሎሶቶዎች ጥንቁቅ ሆነው ኳሶችን ከግብ ክልላቸው እያረቁ ጨዋታውን አጋምሰዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ብሔራዊ ቡድኑ የተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል። ይህኛው አጋማሽ ሲጀምር ይገዙ ቦጋለ ፣ ቸርነት ጉግሳ እና ቢኒያም በላይ ተቀይረው ሲገቡ በዛብህ መለዮ ፣ ሀብታሙ ታደሰ እና ሱለይማን ሀሚድ ደግሞ በተለያዩ ደቂቃዎች ተለውጠው በመግባት ተጫውተዋል። ሌሶቶዎች ይበልጥ ወደ መልሶ ማጥቃቱ ባመዘኑበት በዚህ አጋማሽ ዋልያዎቹ የተሻሉ የማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። ከነዚህም ውስጥ 61ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሀመድ የሰነጠቀለትን ኳስ ቸርነት ጉግሳ በቀኝ መስመር ይዞ በመግባት ወደ ውስጥ የላከውን ሌሶቶዎች ሳያርቁት ቀርተው ይገዙ ቦጋለ በመድረስ ግብ አድርጎታል። ጎሉ ለሲዳማ ቡናው አጥቂ በመጀመሪያ የኢንተርናሽናል ጨዋታው ያስቆጠረው የመጀመሪያ ግቡ ሆኖ ተመዝግቦለታል።
ከአቻነቱ በኋላም ተቀይረው የገቡ ተጫዋቾች ተፅዕኖ ከፍ ሲል ዋልያዎቹ ሁለት ጊዜ ለግብ ቀርበው ነበር። 69ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ የጋቶች ፓኖም ሰንጣቂ ኳስ ይዞ በመግባት ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ሲመለስበት 84ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሱለያማን ሀሚድ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ በግንባሩ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል።
ሌላ ግብ ያላስተናገደው ጨዋታ በ 1-1 ውጤት ሲጠናቀቅ ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በዛው በአዳማ ሳይንስ እና ዩንቨርስቲ ስታዲየም በመጪው ሰኞ ለሁለተኛ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።
ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን ጠቃሚነት አንስተው ከኋላ ጀምሮ ያለው የቡድናቸው አካሄድ ጥሩ ሆኖ ሳለ ተጋጣሚን በማስከፈቱ በኩል ግን ከመጀመሪያው ይልቅ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ መንቀሳቀሳቸውን እና ጨዋታውን ጥሩ ሆኖ እንዳገኙት ገልፀዋል። በጨዋታው እንደ አዲስ ዕድል ስለተሰጧቸው ተጫዋቾች ደግሞ ከብሔራዊ ቡድኑ አጨዋወት ጋር ተቀራራቢ አቅም ያላቸውን ተጫዋቾች ማካተታቸውን እና ዛሬ ባሳዩት እንቅስቃሴም ጥሩ ተስፋ ማየታቸውን በቀጣዩ ጨዋታም ለተጨማሪ ተጫዋቾች ዕድል እንደሚሰጡ ተናግረዋል።