“ሁሉንም መስፈርት በሚያሟላ መልኩ ግንባታው እየተካሄደ ይገኛል።” ክቡር አቶ ከድር ጆሀር (የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ)

በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ግንባታ ዙርያ ከተከበሩ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጆሀር ጋር ቆይታ አድርገናል።

ከዛሬ ሀምሳ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ለምታሰናዳው የአስረኛው የአፍሪካ ዋንጫ መነሻነት ቀድሞ ተሰርቶ የነበረውን ሜዳ የማሻሻያ ስራ ተሰርቶለት ለውድድር ዝግጁ የተደረገው ታሪካዊው የድሬዳዋ ስታዲየም በጊዜ ሂደት የተለያዩ ለውጦች እየተደረጉለት አሁን ያለንበት ጊዜ ደርሷል። አሁን ላይ ሀገራችን በካፍ የፀደቀ ስታድየም የሌላት በመሆኑ ስታዲየሙ ወቅቱ የሚፈልገውን መስፈርቶች በሟላ መልኩ ከሀገር ውስጥ ውድድሮች አልፎ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች እንዲያስተናግድ ለማድረግ የተለያዩ የማስፋፊያ ስራዎች ከጀመረ ሰነባብቷል። በአሁኑ ወቅት ድሬዳዋ ከሌሎች ስታድየሞቻችን ዘመናዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ የካፍን ፎርማሊቲ አሟልቶ እንዲጠናቀቅ ምን ታስቧል ? የሚለውን እና ሌሎች ተዛማች ጥያቄዎችን በመያዝ
ከከተማው ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጆሀር ጋር ሶከር ኢትዮጵያ አጭር ቆይታ አድርጋለች።

ግንባታው አሁን ስላለበት ሁኔታ…

“ኢትዮጵያ የራሷ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ሊኖራት ይገባል በማለት እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ፣ ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ በመውሰድ ጥናት ተጠንቶ ከፍተኛ በጀት በማውጣት ከዓመታት በፊት ግንባታው ተጀመሮ ቀድሞ ባለበት ሁኔታ ግንባታው ተካሂዶ አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል። አሁን አብዛኛው የግንባታ ስራዎች ተጠናቀው መሰረታዊ ወደ ሆኑ ስራዎች እየተሻገርን እንገኛለን።

ከዲጂታል የማስታወቂያ ቦሩዱ እና የስክሪኑ ሥራው ጋር በተያያዘ ስለቀሩ ስራዎች…

“ኢትዮጵያ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ የለም እየተባለ ውድድሮችን ተገደን በገለልተኛ ሜዳ ለማድረግ ችለናል። ይህን ችግር ለመቅረፍ እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር የራሳችንን አስተዋፆኦ መወጣት አለብን ብለን እናስባለን። አስተዋፆ ማድረግ ብቻ ሳይሆን አሁን የተለያዩ ጥረቶችን እያደረግን እንገኛለን። አሁን የገጠምነው እስክሪን ካሜሩኖች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተጠቀሙበት ዘጠኝ በአራት ሜትር አርባ አምስት ካሬ የሆነ በጣም ትልቅ ዘመናዊ እስክሪን ነው። ይህም በኢትዮጵያ ደረጃ ትልቁ እና የመጀመርያው ነው። ከዚህ ውጪ ዲጅታል ማስታወቂያ ቦርዱ ለመስራት ያሰብነው ቆርቆሮዎቹን ፣ ባነሮችን ማስቀረት አለብን በማለት ነው። ሊጉ በ2015 ድሬዳዋ ሲጀመር የተሻለ ነገር ይዘን ለመቅረብ ነው። አሁን ተጀምሯል በጥቂት ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል። ሌሎች ስራዎችም ጊዜያቸውን ጠብቀው እየተሰሩ ይገኛል።

ስለመጫወቻ ሜዳው…

“መጫወቻ ሜዳውን ሙሉ ለሙሉ ሳር ለመቀየር እያሰብን ነው። በተለይ በዕረፍት ሰዓት እና ከጨዋታም በፊትም ሆነ በኋላ አውቶማቲክ ራሱ ውሃ ማጠጣት እንዲችል ማድረግ በተቻለ መጠን ወደ እንቅስቃሴ ገብተናል። ይህም የቀጣይ ዓመት ውድድር ሳይጀምር ተግባራዊ እናደርጋለን። የትኛውንም ውድድር ማስተናገድ እንዲችል ማድረግ እንፈልጋለን። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው አንድ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ካለህ ሁለት የልምምድ ሜዳዎች ማዘጋጀት እንደሚገባ ይታወቃል። በዚህ ላይ አንድ ሰው ሰራሽ ሜዳ እየተሰራ ነው በዚህ ዓመት እንጨርሳለን። ሌላው በተፈጥሮ ሳራ የሚሰራ አለ ጎን ለጎን የሚሰራ ይሆናል። ዋናው ነገር ደረጃውን የጠበቀ ለሀገራችን አሻራ ሆኖ የሚቀር ስራ ለመስራት እየጣርን እንገኛለን።

የካፍን ደረጃ ስለማሟላት…

“ዋናው ጥረታችን ይሄ ነው። እስካሁን ባለው ሁሉንም መስፈርት በሚያሟላ መልኩ ግንባታው እየተካሄደ ይገኛል። ከዚህ በፊት ከካፍ የመጡ ባለሙያዎች በሰጡን ምክረ ሀሳቦች መነሻነት ነው ግንባታው እየሄደ ያለው። የፊፋ ትልቁ መመዘኛ የቪአይፒ ክፍል ፣ የቅድመ ስብሰባ አዳራሽ ፣ የተጫዋቾች መቀየሪያ ክፍል ስታንዳርዱን የጠበቀ አራት መልበሻ ክፍል መኖር አለበት የሚል ነው። ሌላው ለፀጥታ አካላት ሲሲቲቪ ካሜራ ሜዳው ሁሉ እንዲኖረው ነው። ተቀያሪ ተጫዋቾች የሚቀመጡበት ወንበር እንዲሁ መስፈርቱን ያሟላ እንዲሆን አሳይመንት ተሰጥቶናል። እንግዲህ የራሳችንን ስራ እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር ካለው የሀገር ገፅታ ግናባታ አኳያ ነው። ለማንም አይደለም የምንሰራው። በራሳችን አቅም እና በጀት እየሰራን የምንገኘው በተቻለ መጠን የእግርኳስ ኢንቨስትመንት ወደ ድሬዳዋ በማምጣት ከእግርኳሱ የሚገኘውን አቅም ለመጠቀም ነው።”

ያጋሩ