“በጣም ጥሩ ውጤት እንደሚመጣ ላረጋግጥ እወዳለሁ” አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የሴካፋ ውድድር የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 4 በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ እንደሆነ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑ ከሳምንት በፊት ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ በቀን አንድ ጊዜ በ35 ሜዳ ጠንከር ያለ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። ነገ ረፋድ ላይ ወደ ዩጋንዳ ከማቅናቱ በፊት የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ወሎ ሰፈር በሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ ቀትር ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

እምብዛም የሚዲያ አካላት ባልታደሙበት በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ብሔራዊ ቡድኑ በሴካፋ መወዳደሩ ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ ዕቅድ በማውጣት ያከናወኑትን ተግባራት አሰልጣኙ ካብራሩ በኋላ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ለረጅም ዓመት የሚያገለግሉ ወጣቶችን ለማብቃት ውድድሩ ጠቀሜታ እንዳለው በመግለፅ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማስከተል ከጋዜጠኞች ጥቂት ጥያቄዎች የቀረበላቸው ሲሆን የተነሱ ጥያቄዎች እና ምላሾቻቸው እንዲህ ቀርበዋል።

የተመረጡት ተጫዋቾች ከዕረፍት እንደመምጣታቸው በምን ዓይነት ሁኔታ አገኘሀቸው ?

“የሴቶች እና የወንዶች አንድ ዓይነት ዕረፍት አለው ብዬ አላምንም። ሴቶች አራት ፣ ሦሰት ቀን ዕረፍት ሲቀመጡ የሚጨምሩት ኪሎ ይኖራል። በውድድር ላይ ሄጄ ያየኋቸው ልጆች እኔ ጋር ከመጡ በኋላ ሁሉም ሲመጡ በተመሳሳይ አቋም አልመጡም። ወቅታዊ አቋምን መለካት የሚቻለው በኮንትሮል ብቻ አይደለም። እግርኳስ ብዙ ግብአቶች አሉት፣ ልጆቹን ወደ ግብአቱ ለመመለስ ሞክረናል። የተወሰኑ ተጫዋቾች ወደ መስተካከሉ በቶሎ የመጡ አሉ። የተወሰኑት ዘግይተው ወደ ትክክለኛው አቋም የመጡም አሉ፣ አሁንም ድረስ ያልመጡ ልጆች አሉ ያው ባለን ጊዜ ሁሉንም አዋህደን ይዘን እንሄዳለን።

በሴካፋ ዋንጫ የብሔራዊ ቡድኑ ዕቅድ ምንድነው ?

“ሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ቡድን አሸናፊ በመሆን መጥቻለው። ዩጋንዳን አየሩን ፣ ባህሉን ፣ ሜዳውን አቀዋለው። በተጨማሪም ሴካፋ ላይ የሚመጡ ተጫዋቾችን በተወሰነ በመልኩ ከ20 ዓመት በታች የሚመረጡ ሊሆኑ እንደሚችል ላውቅ እችላለው። ያም ቢሆን በዋናው ቡድን ምን ዓይነት ተጫዋቾች ይዘው ይመጣሉ የሚለውን ላላውቅ እችላለው። ለማወቅ ግን ያለብኝ ድረስ ተጉዣለው፣ ቪዲዮችን ሌሎች ነገሮችን ለማየት ሞክሬያለው። እኔ ግን እንደ ነጥብ ይዤ የተነሳሁት ምን ይዤ ልምጣ የሚለውን ሁለተኛ አድርጌው፣ መጀመርያ ግን ይዤ የምጓዘው ለዋናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለረጅም ዓመት ግልጋሎት የሚሰጡ ተጫዋቾችን ጥሩ ነገር እንዲሰሩ ማድረግ ነው። ብዙ ወጣት ተጫዋቾች መጥተዋል። እነዚህን በአራት ዓመት ውስጥ መቀጠል፣ ማስኬድ የሚችል ውጤታማ ቡድን መገንባት ነው። ምስራቅ አፍሪካ ላይ የተሻለ ስም አለን ግን ሁልግዜ ሰሜን፣ ምዕራፍ እና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት እኛን እየተጫኑን የምንቀርበት ጊዜ መጥፋት አለበት። መነሻችንም ይሄ ነው ብዬ ስለማምን ለብዙ ወጣት ተጫዋቾች ቅድሚያ መስጠትን አስባለው። ከዚህ በኋላ ግን ውጤቱ አስባለው። በእግርኳስ ምን እንደሚፈጠር ቀድመው የሚገምቱት አይደለም። ግን ማንም ሰው ውጤት ይፈልጋል። በጣም ጥሩ ውጤት እንደሚመጣ ላረጋግጥ እወዳለሁ።

የተጫዋቾችን አጠቃቀም በተመለከተ

“ሙያ ፈታኝ መሆኑን እጠብቃለው፣ መፈተኑም ጥሩ ነው። ከ20 ዓመት በታች ቡድን ተጫዋቾችን አብዝቼ ያመጣሁበት ምክንያት የቡድኑ ቅንጅት ተስተካክሎ እንዲሄድ፣ ከ20 በታች የነበሩ ልጆች በዋናው ቡድን ቋሚ ሆኖ የሚቀጥሉበት እንዲሆን ነው። በልምድ ደረጃ ከሁለት ያልበለጡ ተጫዋቾች አሉ ቡርቱካን እና ረሂማ ዘርጋው ከዚህ ውጭ ያሉት ሴናፍ፣ ሎዛ፣ ሀሳቤ ሌሎችም ያለ ዕድሜያቸው ቀድመው በመጫወታቸው ልምድ ያግኙ እንጂ ብዙ በእግርኳሱ የቆዩ ልጆች አይደሉም። ስለዚህ አዳዲስ ፊቶች ወደ ብሔራዊ ቡድኑ መጥተዋል። እግርኳስ በዐይን የሚታይ ነው። ለሁለት ከፍለን በማጫወትም፣ በወቅታዊ አቋምም ልጆቹን አይተናል። በጣም መጠበቅ ያለበት በእርግጠኝነት የምነግራቹ በጨዋታ ወቅት አዳዲስ ልጆች ይኖራሉ። ከሰባት እስከ ስምንት ተሰላፊዎች ለወጣቶች ዕድል ይሰጣል።

የተጫዋቾቹ የጤንነት ሁኔታ እንዴት ነው ? ምን ያህል ተጫዋቾችስ ይጓዛሉ ?

“23ቱም ተጫዋቾች እስካሁን ባለኝ መረጃ ሁሉም የሚጓዙ ይሆናል። የጤንነት ሁኔታን በተመለከተ አንድ ልጅ እርስ በእርስ ግጭት ጭንቅላቷ አካባቢ የመተተርተር ሁኔታ አጋጥሟት ተሰፍታለች። ህክምናዋን በአግባቡ ተከታትላ በአሁኑ ሰዓት ሁለት ልምምዶችን ሰርታለች ጥሩ አቋም ላይ ነው ያለችው። ባለሙያዎቹ የሚሰጡኝን ሰምቼ ለጨዋታው ትደርሳለች፣ አትደርስም የሚለውን እወስናለው። እስካሁን ያለችበት አቋም ግን በጣም ጥሩ ነው።”