አዳማ ላይ ከሌሶቶ አቻው ጋር ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንድ አቻ ተለያይቷል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለቱ አጋማሾች ሁለት መልክ የነበረው ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾች ብልጫ ወስደው ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ ቢታይም በ3ኛው ደቂቃ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። በዚህም በ3ኛው ደቂቃ ጊትጋት ኩት ለግብ ጠባቂው በረከት አማረ አቀብላለው ያለውን ኳስ ኃይል እና ከፍታ አብዝቶበት ከግብ ዘቡ በላይ ልኮት መረብ ላይ ለማረፍ ቢቃረብም የግቡ አግዳሚ መልሶታል።
ይህ የራስ ላይ ሙከራ ያላስደነገጣቸው የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ከኳስ ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ በማርዘም መንቀሳቀስ ይዘዋል። በሩብ ሰዓትም በረከት ደስታ ከግራ መስመር ከሽመልስ በቀለ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ጠበቅ ባለ ምቱ ቢልከውም ግብ ጠባቂው ታኒኪሶ ቻባ አውጥቶበታል።
ከኳስ ጀርባ በመሆን ግባቸውን መጠበቅ ላይ ተጠምደው ሲጫወቱ የታዩት ሌሶቶዎች የዋልያው የመከላከል ወረዳ ላይ ተገኝተው ጥቃት መሰንዘር ላይ ተዳክመዋል። በ29ኛው እና በ30ኛው ደቂቃም ሁለት የሰሉ ጥቃቶች በሽመልስ እና ዳዋ አማካኝነት ተሰንዝሮባቸዋል። በ38ኛው ደቂቃ ግን ግባቸውን በሚገባ መጠበቅ ተስኗቸው መመራት ጀምረዋል። በዚህም ከመዓዘን ምት የተነሳውን ኳስ ሔኖል አዱኛ ደርሶት ሲያሻማው በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ዳዋ ሁቴሳ በግንባሩ ከመረብ ጋር አዋህዶታል።
ለተቆጠረባቸው ጎል ወዲያው ምላሽ ለመስጠት ያሰቡት ሌሶቶዎች በ40ኛው ደቂቃ በሱዋሬሎ ቤርጌንግ አማካኝነት በመቱት የቅጣት ምት ግብ ለማግኘት ተቃርበው ለጥቂት ወጥቶባቸዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተለየ ነበር። በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት ተጋባዦቹ በጥሩ ብርታት በመጫወት አቻ ለመሆን ሲታትሩ ነበር። በዋነኛነት ደግሞ የኢትዮጵያ ተጫዋቾችን የኳስ ምስረታ እያጨናገፉ በቀጥተኝነት ግብ ለማግኘት እየጣሩ ነበር።
በዚህ እንቅስቃሴ እየተጫወቱ በ65ኛው ደቂቃ በጃኒ ታባሲቶ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው ተመልሰዋል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሚሊዮን ሰለሞን ወደ መሐል ሜዳ እየገፋ የሄደውን ኳስ ሲሳሳት ተቀይሮ የገባው ሞቴባንግ ሴራ አግኝቶት በቀኝ መስመር እየገፋ ሳጥን ውስጥ ሲገባ ቢኒያም በላይ እና ጋቶች ፓኖም ጥፋት ሰርተው ቡድኑ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። የፍፁም ቅጣቱንም ጃኒ ታባሲቶ ከመረብ ጋር አዋህዶት ቡድኑ አቻ ሆኗል።
አቻ ከሆኑ በኋላም ወደ ግብ መቅረብ የቀጠሉት ሌሶቶዎች በ82ኛው ደቂቃ ሌላ ጥቃት ሰንዝረው ወደ መሪነት ለመሸጋገር ተቃርበው ነበር። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ዳግም ሚሊዮን የተሳሳተውን ኳስ ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሞቴባንግ ሴራ ተረክቦት እየገፋ ሄዶ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ዒላማውን ስቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳስ እና መረብን ቢያገናኝም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሯል። ጨዋታውም አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።