ከሌሶቶ ጨዋታ በኋላ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ መግለጫ ሰጥተዋል

👉”በሁለቱም ጨዋታዎች ለቀዳሚ አሰላለፍ የተጠጋውን ስብስብ በማሰለፍ ማሸነፍ ይቻላል ፤ ግን…

👉”በጨዋታው ከውጤት ይልቅ ተጫዋቾቹን ለማየት ነው የሞከርነው

👉”ስህተቶች በእንደዚህ አይነት ጨዋታዎች ነው እየፀዱ የሚሄዱት

👉”ከሌሶቶ ጋር ያለን አቀራረብ ከግብፅ ወይም ከማላዊ ጋር ይኖረናል ማለት አይደለም

ጨዋታው እንዴት ነበር ?

“ከውጤት አንፃር ከታየ ጨዋታው አንድ ለአንድ ነው የተጠናቀቀው። ይሄ ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያውም ጨዋታ አቻ ነው የተለያየነው። የወዳጅነት ጨዋታ ማድረጋችን ዋናው ነገር ተጫዋቾች ከኢንተርናሽናል ጨዋታ ስለራቁ ያሉበትን ነገር ለማየት ነው። በዛሬው ጨዋታ ደግሞ በመጀመሪያው ጨዋታ ዕድል ያላገኙ ተጫዋቾችን ለማየት ሞክረናል። በሁለቱም ጨዋታዎች ያየናቸው ክፍተቶች አሉ ፤ ባሉት ቀናት እነዚህ ክፍተቶች ላይ ለመስራት እንሞክራለን።

በሁለተኛው አጋማሽ ቡድናቸው ስለመዳከሙ…

“የተለያዩ ተጫዋቾችን ነው ቶሎ ቶሎ ስንቀያይር የነበረው። ይሄም ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው ነገር ግን የሌሶቶዎች አቀራረብ መቀየሩ ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ወረድ ብለው ለመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት መምጣት ላይ በማተኮር ነበር ሲጫወቱ የነበረው ፤ ከእረፍት መልስ ግን በተቃራኒ ከሜዳቸው በጣም ወጥተው እኛን ከሜዳችን እንዳንወጣ ጫና ለማሳደር ሲጥሩ ነበር። ይህንን ጫና ተቋቁሞ መውጣት ላይ መጠነኛ ክፍተቶች ነበሩብን። እነሱም ያንን ነበር ሲጠቀሙ የነበሩት።

በጨዋታዎቹ ስለነበራቸው ዕቅድ…

“28 ተጫዋቾችን ነው የያዝነው። በሁለቱ ጨዋታዎች ያልተሳተፈው አቡበከር ናስር ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ሁሉንም ተጫዋቾች ለመመልከት ሞክረናል። ጨዋታዎቹ የትኛው ተጫዋች ጥሩ ነው የሚለውን እንድናይ ይረዳናል። በተጨማሪም ማን ከማን ጋር ቢጣመር የተሻለ ነገር ያሳያል የሚለውን እንድናይ ይጠቅመናል። በሁለቱም ጨዋታዎች ለቀዳሚ አሰላለፍ የተጠጋውን ስብስብ በማስገባት ማሸነፍ ትችላለህ ግን ለጊዜው ጥቅም የለውም። ተጫዋቾች የጨዋታ ዕድል ማግኘት አለባቸው። እነ ሚሊዮን ምናልባት የመጀመሪያ ኢንተርናሽናል ጨዋታቸው ነው። ከዚህ መነሻነት በጨዋታው ከውጤት ይልቅ ተጫዋቾቹን ለማየት ነው የሞከርነው። ከዚህ አንፃር ያሰብነውን ነገር አይተናል።

በተከላካይ መስመሩ ላይ ስላለው ክፍተት…?

“በተከላካይ መስመሩ ላይ ያለው ክፍተት ከውህደት አንፃር ሳይሆን ከልምድ አንፃር ይመስለኛል። በተለይ በዛሬው ጨዋታ የተሰለፉት ጊት እና ሚሊዮን ለእንደዚህ አይነት ፍልሚያ እንግዳ ናቸው እንጂ ተጫዋቾቹ ያላቸው ብቃት ለጊዜው ለብሔራዊ ቡድኑ በቂ ነው። ስህተቶች በእንደዚህ አይነት ጨዋታዎች ነው እየፀዱ የሚሄዱት። እንደ ሀገር ያሉንን ተጫዋቾች በዚህ መልክ ማቅረብ አለብን እንጂ በተወሰኑ ተጫዋቾች ብቻ ተንተርሶ መጫወት አይኖርብንም። ምክንያቱም እነዛን ተጫዋቾች በተለያዩ ጉዳዮች ልናጣ እንችላለን ፤ ከዚህ አንፃር ተጫዋቾቹን ማየታችን መጥፎ አይደለም። የኋላ መስመሩ ላይ ያሉት ተጫዋቾች እንደ ቡድን ጨዋታ ሲያደርጉ ዛሬ የመጀመሪያቸው ስለሆነ ክፍተቱ የሚጠበቅ ነው።

ስለአቋም መፈተሻው ጨዋታ ጠቀሜታ…

“ከየትኛውም ጨዋታ ጋር ብትጫወት ጨዋታዎቹ ይለያያሉ። ጨዋታ ማግኘት ግን ጥሩ ነው። ትልቅ ጨዋታ ማለት ከእኛ በደረጃ ከፍ ካሉ ቡድኖች ጋር መጫወት ማለት ነው። በሁለቱ ጨዋታዎችም ያገኘነው ፈተና ቀላል የሚባል አይደለም። ያገኘነው ልምድም እንደዛው። ግብፅን የሚመስል ወይም በግብፅ ደረጃ ያለን ቡድን ብንገጥም ጥሩ ነው ግን ይሄም ምንም ማለት አይደለም። ያለችው ቀን አጭር ከመሆኑ አንፃር ከሌሶቶም ጋር ጨዋታ ማግኘቱ ቀላል ነገር አይደለም። ከሌሶቶ ጋር ያለን አቀራረብ ከግብፅ ወይም ከማላዊ ጋር ይኖረናል ማለት አይደለም። ስለዚህ ቢያንስ ግን ከጨዋታው የተወሰነ ለእኛ የሚጠቅም ነገር አለ። ዝም ብለህ ካየከው ግን ከመጫወቻ ሜዳው አንስቶ በብዙ ነገር አይመስልም። እዛ የሚገጥመን ነገር ሌላ ቢሆንም ተጫዋቾቹ ጨዋታ የሚለውን ነገር ማግኘታቸው ጠቃሚ ነው።”

ያጋሩ