አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ዩጋንዳ አይገኙም

በሴካፋ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን የሚመሩት አሠልጣኝ ፍሬው በአሁኑ ሰዓት ከስብስቡ ጋር እንደማይገኙ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በስምንት ቡድኖች መካከል በዩጋንዳ ዛሬ መደረግ እንደጀመረ ይታወቃል። በዚሁ የቀጠና ውድድር ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንም የሀገር ቤት ዝግጅቱን ካጠናቀቀ በኋላ በትናንትናው ዕለት ወደ ስፍራው አቅንቷል። ትናንት አመሻሽ ላይ ጂንጃ ከተማ የደረሰው ቡድኑ ማረፊያውን በፓራዳይዝ ሆቴል ያደረገ ሲሆን ዛሬ ረፋድ ከሦስት ሰዓት ጀምሮ በጂንጃ ትምህርት ቤት ለ50 ደቂቃዎች የቆየ ቀለል ያለ ልምምዱን አከናውኗል።

በዛሬው የልምምድ መርሐ-ግብር ላይ ደግሞ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል አለመገኘታቸውን በስፍራው ከተገኙ የዩጋንዳ የብዙሃን መገናኛ አባላት አረጋግጠናል። ይህንን ተከትሎ ባደረግነው ማጣራት አሠልጣኙ ጉዳዩ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ልዑካን ቡድኑ ትናንት ረፋድ ወደ ስፍራው ሲያቀና አብረው እንዳልተጓዙ አውቀናል። ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስም አሠልጣኙ ቡድኑ ያረፈበት ሆቴል አለመኖራቸውን እና ምናልባት ነገ ቡድኑን ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ ሰምተናል።

ከታንዛኒያ፣ ዛንዚባር እና ደቡብ ሱዳን ጋር የተደለደለው ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ነገ 7 ሰዓት ከዛንዚባር አቻው ጋር እንደሚያደርግ የወጣው መርሐ-ግብር ያሳያል።