በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ለቀጣዮቹ አስር ቀናት የሚከወነው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ውድድር ዛሬ በሁለት ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡
ከአስራ ሁለት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ስምንቱን የሚያሳትፈው የ2022 የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ውድድር በዛሬው ዕለት በዩጋንዳ አዘጋጅነት በፉፋ ቴክኒካል ኒጂሩ ስታዲየም ላይ በሁለት ጨዋታዎች ጅምሩን አድርጓል፡፡ በምድብ አንድ በሚገኙ ሀገራት መካከል በተደረገ ሁለት ጨዋታዎች አዘጋጇ ዮጋንዳ እና ብሩንዲ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ ቀደም ብሎ 7 ሰዓት ላይ በተከወነ የመክፈቻ ጨዋታ ብሩንዲ ጅቡቲን 3ለ0 በሆነ ውጤት ረታለች፡፡ ሳንድሪን ኒዮንኩሩ ፣ ማርያም አህመድ እና ጆይል ቡክሩ የብሩንዲን የድል ግቦች በማስቆጠር ቡድኑን አሸናፊ አድርገዋል፡፡
በመቀጠል 10 ሰዓት ሲል ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ፀሀይነሽ አበበ በመሀል፣ ወይንሸት አበራ በረዳት እንዲሁም ምስጋና ጥላሁንን በአራተኛ ዳኝነት ያሳተፈው የዩጋንዳን እና ሩዋንዳ ጨዋታ አዘጋጇን ሀገር በድል ያስጀመረ ሆኗል፡፡ 2ለ0 በተጠናቀቀው ጨዋታ አጥቂዋ ፋዚላ ኢኪዋፑት ከእረፍት በፊት እና በኋላ ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦች ቡድኗ አሸናፊ እንዲሆን አስችላለች፡፡
ነገ በምድብ ሁለት የምትገኘው ሀገራችን ኢትዮጵያ 7፡00 ላይ ከዛንዚባር ስትገናኝ በምድቡ የሚገኙት ታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን ደግሞ 10 ሰዓት ላይ መርሐ-ግብራቸውን ይከውናሉ፡፡