የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል ሽመልስ በቀለ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት በሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በምድብ አራት ከግብፅ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር የተደለደለ ሲሆን የምድብ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎችን ለማድረግም ከቀናት በፊት ልምምዱን እንደጀመረ ይታወቃል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከሀገር ውጪ የመረጡት ብቸኛው ተጫዋች ሽመልስ በቀለ ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ስብስቡን ተቀላቅሎ ልምምዱን እየሰራ ይገኛል።
ለፔትሮጀት ፊርማውን በማኖር ከስምንት ዓመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በግብፅ እግርኳስ ብቅ ያለው ሽመልስ ዘለግ ላለ ዓመት (ስድስት) በክለቡ ቆይቶ 2019 ላይ ሌላኛውን የሀገሪቱ ክለብ ምስር ለል መቃሳን ተቀላቅሎ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ከወራት በፊት ደግሞ ጉዞውን ወደ አል ጎውና አድርጎ ግልጋሎት እየሰጠ ይገኛል።
በካሜሩን አስተናጋጅነት በተከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ በጉዳት ምክንያት ሀገሩን ያላገለገለው ሽመልስ በቅድሚያ አሁን ስለሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ጠይቀነው ተከታዩን ብሎናል። “በአፍሪካ ዋንጫው ላይ በግሌ ከጡንቻ ጋር ተያይዞ ህመም ነበረብኝ። ማገገም ስለነበረብኝም ጨዋታዎች ላይ ሳልሳተፍ እንደቀረው ይታወቃል። ከዛ በኋላ ግን ክለቤ ውስጥ ካለው የህክምና ባለሙያ ጋር በመሆን ራሴን ወደ ጨዋታዎች መልሻለው። በክለብ ደረጃ ተጫውቻለው። ከትናንት በስትያ የተደረገው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ላይም ተጫውቻለው። ይህ ደግሞ የሚያሳየው ሙሉ ጤንነት ላይ መገኘቴን ነው። አሁን የሚቀጥሉትን ጨዋታዎች በጉጉት እየጠበኩ ነው።”
በትራንስፈር ማርኬት መረጃ መሠረት 68 የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ያደረገው የአጥቂ አማካይ ለአይቮሪኮስቱ የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎችን ለማድረግ የተሰባሰበውን ቡድን “ጥሩ ስብስብ ነው” በማለት በመግለፅ ይህንን ሀሳብ ሰጥቶናል።
“ጥሩ ስብስብ ነው። በተለያየ ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታ ሲኖረው የተለያዩ ተጫዋቾች ይመጣሉ። አሁንም አዳዲስ ተጫዋቾች ቢኖርም ከዚህ ቀደሙ ብዙ የተለየ ነገር አይኖረውም። ያሉት ላይ አዳዲሶቹ ተጨምረው ጥሩ ነገር ለመስራት እየተዘጋጀን እንገኛለን። የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችንም አድርገናል። በተቻለ መልኩ ለመቀናጀት ሞክረናል። በአጠቃላይ ከፊታችን የሚገኙትን ሁለቱን ጨዋታዎች በጥሩ ብቃት እንደምንወጣ አስባለው።”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡን የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች የፊታችን እሁድ እና የነገ ሳምንት ሀሙስ በቅደም ተከተል ከማላዊ እና ግብፅ ጋር ለማድረግ እየተዘጋጀ በሚገኝበት ሰዓት ተጫዋቹም በግሉ እየተዘጋጀ እንደሆነ የገለፀ ሲሆን ጨዋታዎቹ ከሜዳችን ውጪ መደረጉን በማውሳት ከባድ ፈተና ይገጥመናል ይላል።
በግብፅ ሊግ ከ50 በላይ ግቦችን ያስቆጠረ ብቸኛው እና ቀዳሚው ኢትዮጵያዊው የሆነው ሽመልስ “እውነቱን ለመናገር ከሜዳ ውጪ መጫወት በጣም ከባድ ነው። እንኳን ከሜዳ ውጪ በራሳችን ሜዳ ላይም ስትጫወት ተጋጣሚ ቡድኖች በጣም ፈታኝ ሆነው ነው የሚቀርቡት። እንደዚህም ሆኖ ግን እኛም አቅማችንን ስለምናውቀው እና ከሜዳ ውጪ ከጋና ጋር ያደረግነውን ጨምሮ ብዙ ጨዋታዎችን ስላየን ጥሩ ትምህርቶችን አግኝተናል።” በማለት ሀሳቡን አጋርቶናል። በመጨረሻም ተጫዋቹ ከሁለቱ ጨዋታዎች ቢያንስ አራት ነጥቦች ለማግኘት እናስባለን የሚል ንግግሩን አሰምቶን ሀሳቡን ቋጭቷል።