👉 “የግብፅ ጨዋታ የአባይ መነሻ በሆነው ቦታ ላይ ቢደረግ ያለው ትርጉም ግልፅ ነው”
👉”ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ባለመኖሩ ዋጋ እየከፈለ የሚገኘው ፌዴሬሽኑ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ነው”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሩን በሳምንቱ መጨረሻ ከማድረጉ በፊት ዛሬ ከሰዓት የቡድኑን ዝግጅት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። የቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሰጡትን ሀሳብ በቀጣይ ይዘን የምንቀርብ ሲሆን የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከሜዳ ጋር ተያይዞ የሰጡትን አስተያየት በቅድሚያ ይዘን ቀርበናል።
ሀላፊው ተቋማቸው ለቡድኑ ዝግጅት አስፈላጊውን እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ በመግለፅ ንግግራቸውን ጀምረዋል። “ለጨዋታዎቹ እንደ ፌዴሬሽን አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት ዝግጅት እንዲያደርጉ አድርገናል። ቡድኑ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችንም እንዲያደርግ ከሌሶቶ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር አዘጋጅተናል። ቡድናችን ማላዊ ላይ ከማላዊ እና ግብፅ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል። ከግብፅ ጋር ከሜዳችን ውጪ የምንጫወተው በሀገራችን ፍቃድ ያለው ሜዳ ስለሌለ ነው። የሆነው ሆኖ ቡድኑ በሜዳው ሊያደርግ የነበረውን ጨዋታ እዛው ማላዊ ላይ እንዲያደርግ አድርገናል። ይህ የሆነው በዋነኝነት ከወጪ አንፃር ነው። በአንድ ጉዞ ሁለት ጨዋታዎችን አድርገን ለመምጣት በማሰብ ነው ይህንን ውሳኔ የወሰነው። በተጨማሪም ተጫዋቾቹ ከመጀመሪያው ጨዋታ የሚያገግሙበትን መንገድ እና ዝግጅቱን ታሳቢ በማድረግ ለተጫዋቾቹ የሚሆነውን መርጠናል።”
አቶ ባህሩ ቀጥለው “ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ባለመኖሩ ዋጋ እየከፈለ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጽያ ህዝብ ነው” ካሉ በኋላ ቡድኑ በሜዳው ማድረግ የነበረበትን ጨዋታ በሌላ ሀገር በማድረጉ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጣ በአፅንኦት በመግለፅ መንግስት እንዲረዳቸው በአፅንኦት ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚተዳደረው ከፊፋ እና ካፍ ከሚያገኘው ዓመታዊ የገንዘብ ድጎማ ነው። ይህ ዓመታዊ ድጎማ ደግሞ አንድን ተቋም እንደፈለገ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርገው አይደለም። ይህም በቂ ስላልሆነ ከተለያዩ ስፖንሰሮች እና አጋሮች ጋር እየሰራን እንገኛለን። እንደዚህም ሆኖ ይህ በቂ አይደለም። እስካለን ድረስ እየተወዳደርን ነው። ግን ከውድድር የመውጣትም ነገር ሊመጣ ይችላል። ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እንዳለብን ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርበናል። መንግስት ሊያግዘን ይገባል።
“የግብፅን ጨዋታ ማላዊ ላይ ለማድረግ 50 ሺ ዶላር ያስፈልገናል። ይህ ገንዘብ የአውሮፕላን ትኬት፣ አኮሞዴሽን፣ ለስታዲየም ኪራይ፣ ስቲዋርድ፣ ፖሊስ፣ የልምምድ ሜዳ ኪራይ፣ አጃቢ፣ አምቡላንስ፣ ለዳኞች ማረፊያ ሆቴል፣ የተጫዋች አበል እና ተያያዥ ወጪዎችን ሳያካትት ነው። በነገራችን ላይ ከማላዊ የጤና ጥበቃ የጠየቅነው ፍቃድ አዎንታዊ ምላሽ ካገኘ ከሜዳ የሆነ ነገር ለማግኘት ጨዋታው ለተመልካች ክፍት ለማድረግ እናስባለን። በዚህም ስታዲየሙ ከሚይዘው ግማሽ ለማስገባት እየጣርን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ፒች ሳይድ ማስታወቂያ እንዲኖር እና ወደ 2500 ዶላር ለማግኘት ከአንድ ተቋም ጋር እየተነጋገርን ነው። ከላይ የጠቀስናቸው ወጪዎች ሀገራች ላይ ቢሆን በሀገራችን ገንዘብ ነበር የሚፈፀሙት ፤ አሁን ግን በውጪ ምንዛሬ ነው የምንከፍለው።”
በመጨረሻም “ይህ ጨዋታ የአባይ መነሻ በሆነው ቦታ ላይ ቢደረግ የያለው ትርጉም ግልፅ ነው።” ካሉ በኋላ የግብፅ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሙሉ ወጪያችንን ችሎን ካይሮ ላይ እንድንጫወት ጠይቆን ክብረ ነክ ነው ብለን መልሰነዋል የሚል ሀሳባቸውን ገልፀው ንግግራቸውን አገባደዋል።