👉 “የብሔራዊ ቡድኑ ጉዳይ እንደማያሳስበው ሲናገር ሰምቻለሁ”
👉 ” ከዚህ በላይ ለልጄ እንኳን ‘ፖዘቲቭ’ የምሆን አይመስለኝም”
👉 “ከኔ ጋር ቢጣላ እንኳን ስራውን መስራት ነው የነበረበት”
ዛሬ ከምሳ በኋላ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ዋሊያዎቹ በቀጣይ ቀናት የሚያደርጓቸውን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በተመለከ በተሰጠው ሰፊ መግለጫ ላይ ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ በብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና በተጫዋች ጌታነህ ከበደ መካከል የተፈጠረውን ክፍተት የተመለከተው ጉዳይ ነበር። በ13 ግቦች ከይገዙ ቦጋለ ጋር በጣምራ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን በመምራት ላይ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ በብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ውስጥ አለመካተቱ ከሰሞኑ ሲያወዛግብ ቆይቷል። ይህንን አስመልክቶም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አሰልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑ ለልምምድ ለውስን ጊዜ የሚገናኝ እንደመሆኑ ረጅሙን ጊዜ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ አርባ የሚደርሱ ተጫዋቾችን በመዘርዘር በሊጉ ጨዋታዎች ላይ የሚያሳዩትን አቋም በመመዘን እና በመከታተል እንደሚያሳልፉ በማስረዳት መልሳቸውን ጀምረዋል። ከጅምሩ ኃላፊነት ከመረከባቸው በፊት በነበረው የኮትዲቯሩ ጨዋታ ላይ ጌታነህ እንዳልነበረ እና ወደ ብሔራዊ ቡድን የመለሱት እሳቸው መሆናቸውን በማስታወስ በቀጣዮቹ ጊዜያት እንደ አምበል የሚጠበቅበትን ከማድረግ ባለፈ ግቦችንም በማስቆጠር ኃላፊነቱን መወጣቱን እንዲሁም በክለቡ የዲስፕሊን ቅጣት ተላልፎበት በነበረበት ወቅትም ጠርተውት ተመሳሳይ ግልጋሎት መስጠቱን አስረድተዋል።
በመቀጠል በአሰልጣኙ እና በተጫዋቹ መካከል የተፈጠረው ክፍተት ከካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ መልስ ያሳለፈውን ሂደት እንዲህ ሲሉ ገልፀዋል። “ከካሜሩን መልስ አንድ የወዳጅነት ጨዋታ አድርገናል። ጌታነህ ያልተመረጠበት ጨዋታ ይህ የኮሞሮስ ጨዋታ ነው። በዚህ ጨዋታ ጌታነህን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ነባር ተጫዋቾችንም ትተን ሌሎች ልጆችን ለማየት ነው የሄድነው። ከዛ በኋላ ከጨዋታ በኋላ በተደረገ አንድ ቃለ ምልልስ ላይ ስለብሔራዊ ቡድኑ የሰጠው አስተያየት ነበር። ስለብሔራዊ ቡድን ለማውራት ለጊዜው ዝግጁ እንዳልሆነ ፣ ሀሳቡ ክለብ ላይ እንጂ የብሔራዊ ቡድኑ ጉዳይ እንደማያሳስበው ሲናገር ሰምቻለሁ። ያንን ተከትሎ ደውዬ ለማነጋገር ሙከራ አድርጌያለሁ። ከዛ በኋላ እኔ እና ጌታነህ መገናኘት አልቻልንም ፤ በተደጋጋሚ ጊዜ ደውያለሁ። ”
አሰልጣኙ ማብራሪያቸውን በመቀጠል ከብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ጋር የሚገናኙበት የቴሌግራም ግሩፕ ያለ መሆኑን ከዛ ውጪ ደግሞ በግል ስልክ በመደወልም ከተጫዋቾች ጋር እንደሚነጋገሩ አስረድተው ጌታነህ በተደጋጋሚ ደውለውለት እንዳልመለሰላቸው አስረድተዋል። ከስልክ ባለፈ ስላደረጉት ጥረት እና ስላገኙት ውጤትም ይህንን ብለዋል። “የመጨረሻውን ጥሪ ከማድረጌ በፊት ባህር ዳር ነበርን (የአሰልጣኝ ቡድን አባላት) ትኬት ሰርዤ ድጋሚ ለማግኘት ሞክርያለሁ ፤ ግን አልተሳካም። ስለዚህ በዚህ በኩል ለመጫወት ፍቃደኛ አለመሆኑን በግልፅ በሚመስል መልኩ የሰጠው መግለጫ አለ ፣ እንዳገኘውም ፍቃደኛ አይደለም ፣ ዘግይቶ እንኳን ስልኬን ለመመለስ ፍቃደኛ አይደለም። ስለዚህ አብሮ ለመስራት አንድ የጎደለው ወይም የያዘው ነገር እንዳለ ነው የሚሰማኝ።”
ጌታነህ ከበደ እስካሁን ከነበረው ግልጋሎት ፣ ከነባር ተጫዋችነቱ አንፃር ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጡት እና ከእሱ ብዙ ነገር ይጠብቁ እንደነበር ያነሱት አሰልጣኙ አብሮ ለመስራት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ምርጫው እንዳለፈው ጠቁመዋል። በመቀጠል ብሔራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት በመሩባቸው ጊዜያት ተጫዋቹ ላይ ስለነበራቸው አቋም እና አሁናዊ አመለካከታቸው ሲያስረዱ ” 13 ጎል ማግባቱ ግልፅ ነው ፤ ባላገባበት ሰዓትም መርጬዋለው። ያ ብቻ አይደለም ‘በዘጠኝ ቁጥር ቦታ 29 ጎል ያገባው አቡበከር እያለ እንዴት ጌታነህ ይጫወታል ?’ የሚል ጥያቄ ሲመጣ ምን ያህል ለጌታነህ አቅም እና ችሎታ ክብር እና ቦታ እንዳለኝ ለማሳየት ሞክሪያለሁ። ከዚህ በላይ ለልጄ እንኳን ‘ፖዘቲቭ’ የምሆን አይመስለኝም። የሚቻለውን ነገር ለማድረግ ሞክረናል ፤ ያንን ነገር ‘አቢውዝ’ አድርጎታል ብዬ ነው የማስበው። ከዚያ በኋላ በአንድ የስልክ ጥሪ ጥያቄ ማቅረብ ፣ ቅሬታም ካለው ቅሬታውን ሊገልፅልኝ ይችል ነበር። ያ አልሆነም ፤ በዛ ምክንያት ዘለነዋል። ” ብለዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከተጫዋቹ ጋር የተፈጠረውን ክፍተት ከዲስፕሊን አንፃር እንደሚመለከቱት ጭምር ያስረዱበት የመጨረሻ ሀሳባቸው ደግሞ ይህንን ይመስል ነበር። “እኔ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኙ ነኝ ፤ እሱ አምበል ነው። ለእሱ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች የሚሄዱ መልዕክቶች ራሱ በእሱ በኩል ነው የሚሄዱት። ስለዚህ ስልኬን አንዴ እንኳን ባያነሳ ወይም ባይመቸው መልሶ ሊደውል ይገባዋል። ይሄንን ቢያንስ ላለፈው አንድ ወር ገደማ አድርጌዋለሁ። ስለዚህ ዲስፕሊን ማለት የግድ ጠጥቶ ማደር ወይም ሌሎች ነገሮችን ማድረግ ብቻ አይደለም። ከዚህ አንፃር አብሮ ለመስራት ፍቃደኛ አይደለም ፣ ስልክ ለመመለስ ፍቃደኛ አይደለም ፣ ይሄን የብሔራዊ ቡድን አርማ እጁ ላይ አድርጎ እዛ ቦታ ላይ ሲገኝ ከአሰልጣኙ እና ከተጫዋቾቹ ጋር ተቀራርቦ ሊያግለግል ጭምር ነው ኃላፊነት የሚወስደው። ነፃ ፍቃድ ወይም አስገዳጅ ቢሆንም ይህንን ትስስር መበጠስ አልነበረበት። ከኔ ጋር ቢጣላ እንኳን ስራውን መስራት ነው የነበረበት። “