👉”ሁለቱ ጨዋታዎች አፍሪካ ዋንጫ የመግባት ኃይላችንን ሊወስኑ ይችላሉ ፤ ነገር ግን የእኔን ቀጣይነት ሊወስኑ አይችሉም”
👉”ግብፅን በህዝባችን ፊት ብንገጥማት ጥሩ ነበር”
👉”በምድባችን ተራ ተገማቾች ነን ብለን አናስብም”
👉”‘ዕጣ ፋንታው በሁለቱ ጨዋታዎች ነው የሚወሰነው’ የሚባለውን አልቀበለውም። ሲጀምር ዕጣ ፋንታ የሚወሰነው በፈጣሪ ነው”
አይቮሪኮስት በምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የአህጉራችን የማጣሪያ ጨዋታዎች በትናንትናው ዕለት የተጀመሩ ሲሆን በምድብ አራት ከማላዊ፣ ግብፅ እና ጊኒ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በሳምንቱ መጨረሻ የምድብ ጨዋታዎቹን ማድረግ የሚጀምር ይሆናል። የቡድኑን ዝግጅት አስመልክቶ ደግሞ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ከሰዓት በርካታ የብዙሃን መገናኛ አባላት በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በቅድሚያም አሠልጣኙ የዝግጅት ጊዜያቸውን አስመልክቶ ገለፃ በማድረግ ሀሳብ መስጠት ይዘዋል።
“ዝግጅታችንን ከግንቦት 16 ጀምሮ ማድረግ ጀምረናል። በቅድሚያ ለ28 ተጫቾች ጥሪ በማድረግ ወደ ልምምድ የገባን ሲሆን 2 የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችንም ከሌሶቶ ጋር አድርገን የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን ለይተናል። በአቋም መለኪያው ጨዋታ ዳዋ ሁቴሳ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት ነበር። አሁን ግን ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ልምምድ ተመልሷል። አቡበከር ናስር ደግሞ ከክለቡ ሲመጣ መጠነኛ ጉዳት ነበረው። እርሱም የጂምናዚየም ሥራዎችን ሲሰራ ከቆየ በኋላ አሁን ሙሉ ልምምድ ጀምሯል።
“እንደገለፅኩት ለውድድሩ እንዲረዳን ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርገናል። በጨዋታዎቹ ከ2 ተጫዋቾች ውጪ (ሰዒድ ሀብታሙ እና አቡበከር ናስር) ያሉትን ተጫዋቾች ወቅታዊ ነገር ለማየት ሞክረናል። ከውጤት አንፃር ጨዋታዎቹን ማሸነፍ ባንችልም ጠንካራ እና ደካማ ጎናችንን አይተን ለቀጣዮቹ ጨዋታዎች እየተዘጋጀን ነው። አሁን እንደ ከዚህ ቀደሙ ረጅም ጊዜ የመዘጋጀት ነገር የለም። አጭር የዝግጅት ጊዜ ነው ያለው። ይህንን በመንተራስ ከ28 ተጫዋቾች ቀድመን ወደ 40 የሚጠጉ ተጫዋቾችን ለይተን እየተከታተልን ተጫዋቾቹ እዛው ቡድናቸው ላይ እያሉ የሚገኙበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለማየት ሞክረናል።”
ሀገራችን ኢትዮጵያ በካፍ ውድድሮችን በሜዳዋ ማድረግ እንዳትችል ፍቃድ መከልከሏን ተከትሎ ብሔራዊ ቡድኑ ከግብፅ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማላዊ ላይ እንደሚያደርግ ይታወቃል። ይህንን አስመልክቶ “ከባድ ፈተና” በማለት የገለፁት አሠልጣኙ ከሜዳቸው ውጪ ቢጫወቱም ጥሩ ውጤት ለማምጣት እየተዘጋጁ እንደሆነ አስረድተዋል።
“ይሄ ለእኛ ከባድ ነው። ከመጣን ጀምሮ ያለው ነገር ከባድ ነው። ልክ ወደ ቦታው ስመጣ በኮቪድ ያለ ደጋፊ ስንጫወት ነበር። ባለፈውም ጋናን ከሜዳችን ውጪ ሄደን ገጥመናል። ይሄ ከባድ ፈተና ነው። ጥሩ ተጫውተን አቻ ወጥተን ነበር። አሁንም ተመሳሳይ ፈተና ገጥሞናል። ግብፅን በህዝባችን ፊት ብንገጥማት ጥሩ ነበር። ነገርግን አልተቻለም። ያለውን ነገር ተቀብለን የምንችለውን ሁሉ ነገር እናደርጋለን።”
በተከታይነት ለአይቮሪኮስቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የተደለደሉበትን ምድብ በተመለከተ “ምድቡ ላይ ከሚገኙት ቡድኖች 3ቱ ያለፈው አፍሪካ ዋንጫ ላይ ነበሩ። ግብፅ ያለችበት ደረጃ ደግሞ ይታወቃል። ጊኒም እንደዛው። ከዚህ ምድብ ግብፅ የተሻለ እድል ያላት እንደሚሆን ወረቀት ላይ መገመት ይቻላል። ነገርግን እኛ ከ3ቱም ጋር ስንጫወት ያለውን ነገር ተቆጣጥረን ያለውን ስጋት ቀንሰን ጥሩ ነገር ለማምጣት እንሞክራለን። ቡድናችንም አብሮ የቆየ ቡድን መሆኑን በመንተራስ ከምድባችን ለማለፍ የሚቻለውን ሁሉ ለማሳካት ጥረት እናደርጋል። በአጠቃላይ ዓላማችን ከምድባችን ማለፍ ነው። ከሁለቱ ጨዋታዎች ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሳልፈንን ነጥብ ለማግኘት እንሞክራለን። በምድባችን ግን ተራ ተገማቾች ነን ብለን አናስብም።” የሚል ሀሳባቸውን ከሰጡ በኋላ ከተጫዋች ምርጫ ጋር ተያይዞ ለሚነሳው ጥያቄ ደግሞ ይህንን ብለዋል።
“በሊጉ በወጥነት የሚጫወቱ ተጫዋቾች ማግኘት ከባድ ነው። በሌሎቹ ሊጎች በቋሚነት እና በወጥነት ሁሉንም ጨዋታዎች ያደረጉ ተጫዋቾች ማግኘት ቀላል ነው። እኛ ጋር ግን ይህ ከባድ ነው። ውስጣችን ያለው ፍላጎት የነበረውን ነገር ለማስቀጠል በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙትን መያዝ የሚል ነው። ቀድሜ እንዳልኩት ደግሞ ገና 28 ተጫዋቾችን ሳንጠራ ወደ 40 የሚጠጉ ተጫዋቾችን ለይተን ያላቸውን ነገር ከባለሙያዎች ጋር በመሆን ለማየት ተሞክሯል። 28ቱ ውስጥ ገብተው ደግሞ የተቀነሱትን በተመለከተ በአቋም መፈተሻ ጨዋታዎቹ እና ልምምዶቹ በአይን የሚታዩ እና ቁጥሮች የሚሉትን ነገር ለማየት ሞክረናል። የተቀነሱት ተጫዋቾች ግን ለቡድኑ በቂ አይደለም ማለት አይደለም።” ብለዋል።
ከሦስት ወራት በኋላ በብሔራዊ ቡድኑ መንበር ሁለት ዓመት የሚሞላቸው አሠልጣኙ ከቡድን እድገት ጋር በተያያዘ ጥያቄ ቀርቦላቸው ከእኔ በላይ የሚያይ ሰው እድገቱን ይናገር የሚል ይዘት ያለው ምላሽ ሰጥተዋል። “ከእኔ በላይ ስለቡድኑ ሌላ ሰው መናገር ቢችል ጥሩ ነው። ነገርግን አድጓል ካልንስ ከየትኛው ቡድን ጋር አወዳድረን ነው። ከራሳችን ጋር ከሆነ ከእኔ በፊት ያለው እና እኔ ከመጣው በኋላ ያለውን ማየት ነው። እንደ እኔ ግን ትንሽ መስመር የያዙ ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል። እንደ አጠቃላይ ግን ከማሸነፍ መሸነፉ ውጪ እየተገነባ ያለው ነገር እና ካለው ሥነ-ልቦና ጋር ያደገ ነገር ያለ ይመስለኛል።” ብለው በመመለስ በውላቸው ማብቂያ መባቻ ላይ እንደመገኘታቸው በቀጣይ ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ነገሮች ተጠይቀው ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
“ወደዚህ ቦታ ስመጣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የተነጋገርነው ነገር አለ። አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ እና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ 10 ውስጥ መግባት የሚል ነው። ከተጫዋቾቹ ጋር ደግሞ ከአጨዋወት እና ውጤት አንፃር ያስቀመጥነው ግብ አለ። አብዛኞቹን ነገሮች አሳክተናል ብዬ አስባለው። ቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች አፍሪካ ዋንጫ የመግባት ሀይላችንን ሊወስኑ ይችላሉ ነገርግን የእኔን ቀጣይነት ሊወስኑ አይችሉም። እንደተባለው መስከረም ላይ ውሌ ያልቃል። ነገርግን ስለ ቀጣይ ነገሮች ፌዴሬሽኑ ብቻ አይደለም ወሳኝ። እኔም መብት አለኝ። ‘እጣ ፋንታው በሁለቱ ጨዋታዎች ነው የሚወሰነው’ የሚባለውን አልቀበለውም። ሲጀምር እጣ ፋንታ የሚወሰነው በፈጣሪ ነው። በሁለት ጨዋታ ብቻ አንድ አሠልጣኝ ይገመገማል ማለት ከባድ ነው። ዋናው ምን ለመስራት አቅደን ምን ሰርተናል የሚለው ነው።”
በመጨረሻም በዝግጅታቸው እንደ ተግዳሮት የሚነሳው በሜዳቸው አለመጫወታቸው እንደሆነ ሳይሸሽጉ ተናግረው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ቡድኑ የራሱ ስለሆነ ድጋፍ እና ማበረታቻ እንዲሰጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።