የሰበታ እና የተጫዋቾቹ ጉዳይ አልተፈታም

የሰበታ ተጫዋቾች ከደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ ልምምድ ያልጀመሩ ሲሆን ክለቡም በተጫዋቾቹ ላይ ማስታወቂያ አውጥቷል።

በዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በወራጅ ቀጠናው እየዳከረ የሚገኘው ሰበታ ከተማ በቀሪ አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ራሱን አጠናክሮ ካለበት የመውረድ ስጋት ለመላቀቅ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ተብሎ በሚጠበቅበት ሰዓት ከደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ 20 ተጫዋቾቹ እስካሁን ልምምድ እንዳልጀመሩ ተሰምቷል። እርግጥ ከቀናቶች በፊት እንደዘገብነው 21 የክለቡ ተጫዋቾች ደመወዛቸው ካልተከፈላቸው በልምምድም ሆነ በውድድር ላይ እንደማይካፈሉ ገልፀው ነበር።

ሰኔ 7 ባህር ዳር ላይ ለሚጀምረው ውድድር ከሦስት ቀናት በፊት ግንቦት 23 በውድድሩ ስፍራ በሚገኘው ሌክ ማርክ ሆቴል ተጫዋቾች እንዲገኙ ክለቡ ጥሪ ቢያስተላልፍም መገኘት ከነበረባቸው 27 ተጫዋቾች ጥሪውን አክብረው የተገኙት 7ቱ ብቻ እንደሆኑ አውቀናል። በስፍራው ያልተገኙት ተጫዋቾች ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ተከትሎ እንደሆነ ግልፅ ቢሆንም ክለቡ ደግሞ በተቃራኒ በ20’ዎቹ ተጫዋቾች ላይ ማስታወቂያ ማውጣቱን ተረድተናል። በትናንትናው ዕለት በወጣው የክለቡ ማስታወቂያ ላይም በሆቴሉ ያልተገኙት ተጫዋቾች ስማቸው ተዘርዝሮ እስከ ፊታችን ቅዳሜ 6 ሰዓት ድረስ ሪፖርት እንዲያደርጉ ያመላክታል።

የተጫዋቾቹን የደመወዝ ጥያቄ በተመለከተ ክለቡ ያለውን ምላሽ እንዲሰጡን ያናገርናቸው ሥራ አስኪያጁ አቶ አለማየሁ ምንዳ “ክለቡ የተጫዋቾቹን ጥያቄ ለመመለስ እየጣረ ይገኛል። የክለቡ ቦርድም የተለያዩ የገቢ ማግኛ ዘዴዎችን እየተከተለ በጀት ለመሰብሰብ እየሞከረ ነው። በዚህም እስከ ሰኔ አጋማሽ ድረስ ተጫዋቾቹ ያላቸውን ሙሉ ደመወዝ የምንፈፅም ይሆናል።” ካሉን በኋላ ተጫዋቾቹ በወጣው ማስታወቂያ መሰረት ሪፖርት እንዲያደርጉ ካልሆነ ግን ክለቡ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ጠቁመዋል።