የማላዊ ሀገር መሪዎች ከ27 ዓመታት በኋላ እሁድ ስታዲየም ይገኛሉ

ከነገ በስትያ ነበልባሎቹ እና ዋልያዎቹ የሚያደርጉትን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ የማላዊ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ስታዲየም ተገኝተው ይመለከቱታል።

በቀጣዩ ዓመት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር አይቮሪኮስት የሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ከነገ በስትያ ማድረግ ይጀምራል። የምድብ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ማላዊ ዛሬ ያቀናው ብሔራዊ ቡድኑ በሀገሪቱ ርዕሰ መዲና ሊሎንግዌ ሰን በርድ ሆቴል ማረፊያውን አድርጓል። የማላዊ አቻውም በቢሾፕ ማኬንዚ ስፖርት ኮምፕሌክስ ልምምድን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ቀትር ላይ ወሳኝ ተጫዋቹን ፒተር ባዳርን በጉዳት እንዳጣ አስነብበን ነበር። ከደቂቃዎች በፊት የማላዊ መንግሥት የፕሬስ ሴክሬተሪ እንዳረጋገጡት ከሆነ ደግሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሳሎስ ቺሊማ የእሁዱን ጨዋታ ስታዲየም ተገኝተው ይከታተላሉ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ፕሬዝዳንት በይፋዊ የነጥብ ጨዋታ (ሐምሌ 6 ከሚከበረው የነፃነት ቀን የወዳጅነት ጨዋታዎች ውጪ) ስታዲየም ተገኝቶ ብሔራዊ ቡድኑን የሚመለከተው ከ27 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ለመጨረሻ ጊዜ እንደ አውሮፖዊያን አቆጣጠር ከ1994-2004 ድረስ ሀገሪቷን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ባኪሊ ሙዙሊ 1995 ላይ በካሙዙ ስታዲየም ብሔራዊ ቡድኑ ከደቡብ አፍሪካ እና ካሜሩን ጋር ያደረገው እና የተሸነፈበትን ጨዋታዎች ነበር የተመለከቱት። ከሙዙሊ በኋላ በመንበሩ የነበሩት ቢንጉ ዋ ሙታሪካ፣ ጆይስ ባንዳ እና ፒተር ሙታሪካ አንድም ጊዜ የነበልባሎቹን ጨዋታ ስታዲየም ተገኝተው አልተከታተሉም ነበር።

2020 ላይ ወደ ሥልጣን የመጡት የ67 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ቡድኑ በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፉን ሲያረጋግጥ በቤተ-መንግስታቸው ጋብዘው እንዳበረታቱ እንዲሁም ለቡድኑ የገቢ ማሰባሰቢያ የራት ግብዧ አዘጋጅተው እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። በተጨማሪም የሴቶች ብሔራዊ ቡድኑም በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተከናወነው የኮሳፋ ውድድር ላይ ባስመዘገበው ውጤት ተደስተው ግብዧ አሰናድተው ነበር። አሁን ደግሞ የቡድኑን አባላት ለማበረታታት ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረገውን ጨዋታ ከምክትላቸው ጋር ስታዲየም ተገኝተው ለማየት እንደወሰኑ ተሰምቷል።

በተያያዘ ዜና የማላዊ የስፖርት ሚኒስተር ሪቻርድ ቺምዌንዶ ባንዳም በትናትናው ዕለት ብሔራዊ ቡድኑን በመጎብኘት የበጀት እጥረት እንዳይኖር መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ እንደተናገሩ ተመላክቷል።