የዋልያዎቹ አሰልጣኝ እና አምበል ከነገው ጨዋታ በፊት አስተያየት ሰጥተዋል

ዋልያዎቹ ነገ ከማላዊ ጋር የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ሲጠበቅ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ ሽመልስ በቀለ ከመገናኛ ብዙሀን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

ስለዝግጅት ጊዜያቸው እና ስለተጋጣሚያቸው…

“ከምድብ ድልድሉ ለመጀመር በጠንካራ ምድብ ውስጥ መሆናችንን እናውቃለን። ከጁን 25 ጀምሮ ለማጣሪያው ስንዘጋጅ ቆይተናል። ተጫዋቾቻችን ያሉበትን ደረጃ ለመመዘን ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን አድርገናል። ከሌሶቶ ጋር ያደረግናቸውን እነዚህን ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቀናል። ከጨዋታዎቹ በኋላ የስብስባችንን ቁጥር ከ28 ወደ 23 ቀንሰናል። በዚህም ለመጀመሪያው የማላዊ ጨዋታ ዝግጁ ሆነናል። ማላዊ ጥሩ ቡድን ነው። በመጨረሻው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏቸውም ጥሩ ነበሩ ፤ ከምድባቸው ማለፍ ችለው ነበር። ሁሉንም ተጋጣሚዎቻችንን እናከብራለን። ማላዊዎች ጥሩ ጥሩ አጥቂዎች እንዳሏቸው እና ቀጥተኛ እግርኳስን እንደሚጫወቱ እናውቃለን። ነገር ግን ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ አሳክተን ለመውጣት እንጫወታለን።

ስለምድቡ…

“የማጣሪያውን የምድብ ድልድል ስንመለከተው የእኛ ምድብ ጠንካራ ነው ፤ ምክንያቱም ሁላችንም በመጨረሻው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ተካፍለናል። እንደሚታወቀው ግብፅ ሁለተኛ ሆና መጨረስ ችላ ነበር ፤ ጠንካራ ቡድንም አላት። ማላዊ እና ጊኒም እንዲሁ ከምድባቸው ማለፍ ችለው ነበር ፤ እኛም ጥሩ ስብስብ አለን። በመሆኑም ምድቡ ጠንካራ ነው። አንዱ ቡድን በቀላሉ ያልፋል ብሎ መናገር የሚቻልበት አይደለም።”

ስለተጫዋቾች ዝግጁነት…

“ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው። አንድ ተጫዋች ብቻ መጠነኛ ጉዳት ነበረበት። አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ልምምዱን በአግባቡ መስራት ችሏል።”

ስለብሔራዊ ቡድኑ ወቅታዊ አቋም…

“በእርግጥ ካለፉት ጥቂት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ነው ማሸነፍ የቻልነው። ሆኖም ጥሩ ተንቀሳቅሰናል ፤ ቡድናችንን በጥሩ ሁኔታ በማዋቀር ላይ ነን። ከዚህ በፊት ከነበርንበት አንፃር ጥሩ መሻሻሎችን አድርገናል። በመሆኑም የተሻለ ውጤት እንጠብቃለን።”

ሽመልስ በቀለ

“ጥሩ ብሔራዊ ቡድን እና ጥሩ አሰልጣኝ አለን። ስለተጋጣሚ ቡድኖች ከመናገር ይልቅ የነገውን ጨዋታ መጠበቅ የተሻለ ይሆናል። በሜዳው ላይ እስካሁን ልምምድ አልሰራንም ፤ አየሩ ግን በመጠኑ ቀዝቀዝ የሚል ነው። ሆኖም ከህገራችን ጋር ተመሳሳይ ነው። በነገው ጨዋታ ላይ ደግሞ የምናየው ይሆናል።”