የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ አጥቂ የሆነው አቡበከር ናስር ከነገው ጨዋታ በፊት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የምድብ ማጣሪያ ጉዞውን ነገ የሚጀምር ሲሆን ቡድኑ ከማላዊ እና ግብፅ ጋር ለመፋለም ትናንት ረፋድ ወደ ስፍራው (ሊሎንግዌ) አቅንቶ ጨዋታዎቹን እየተጠባበቀ ይገኛል። ዋሊያው ወደ ስፋራው ከማቅናቱ በፊት ደግሞ የስብስቡን ወሳኝ ተጫዋች አቡበከር ናስር አግኝተን አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንድ የውድድር ዓመት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው አቡበከር ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና በ17ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲጫወት ጉዳት አስተናግዶ ከህመሙ ጋር እየታገለ ሲጫወት እንደነበረ አይዘነጋም። ተጫዋቹ በብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከተጠራ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያ የልምምድ መርሐ-ግብሮች ላይ ሙሉ ለሙሉ ሲሳተፍ ያላየነው ቢሆንም ከአቋም መፈተሻዎቹ ጨዋታዎች በኋላ ግን በሚፈለገው ልክ አገግሞ ልምምዶችን ሲጨርስ አስተውለናል። አሁን ጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የሚናገረው ተጫዋቹ ልምምድ ሲሰራ ያልነበረው ራሱን ከከፋ ጉዳት ለመጠበቅ ታስቦ እንደሆነ ይገልፃል።
ገና በሀያዎቹ እድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው እና ለክለቡ እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች የሆነው አቡበከር በቅድሚያ የዝግጅት ጊዜያቸውን አስመልክቶ ተከታዩን ብሎናል። “ዝግጅታችን ጥሩ ነው። የአቋም መፈተሻ ጨዋታም አድርገናል። የሁለት ሰዓት አጠቃላይ የአራት ሰዓት ጉዞ አድርገን ተጫውተናል። እየተመላለስን መጫወታችን ትንሽ አድካሚ ነበር። ግን ጨዋታዎቹ ጠቃሚ ናቸው ብዬ ነው የማስበው። ቡድኑ ውስጥ የዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ያላደረጉ አዳዲስ ተጫዋቾች ስላሉ አሠልጣኞቹ እነሱን ለማየት ተጠቅመውበታል።”
በነገው ጨዋታ የቡድኑ የአጥቂ መስመር አጋፋሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው አቡበከር በማስከተል 23 ተጫዋቾች ስለሚገኙበት ስብስብ ይህንን ይላል። “ስብስባችን በጣም አሪፍ ነው። ልምምዳችንን ከግንቦት 17 ጀምሮ መስራት ይዘናል። የቡድን መንፈሱም ጥሩ የሚባል ነው። ሁለቱም ጨዋታዎች ከሜዳችን ውጪ ናቸው። ጨዋታዎቹ ሰው ሜዳ ቢሆኑም ወደ ስፍራው የምንሄደው ለማሸነፍ ነው። ይሄም ደግሞ ይሳካል ብዬ አስባለው።”
በመጨረሻም ብሔራዊ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች አስመልክቶ ሀሳብ ያጋራን አቡበከር ከግብፅ ጋር የሚደረገው ጨዋታ በሜዳችን ቢሆን የሚኖረውን ድባብ ጠቅሶ ከሜዳም ውጪ የሚኖረውን ፈተና ተቋቁመው ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚጥሩ ይናገራል።
“በሜዳ ላይ መጫወት ጥቅም አለው። ሜዳችን ላይ ከግብፅ ጋር ብንጫወት ኖሮ በጣም ጥሩ ነው። ፖለቲካውም ስላለ ህዝቡ በደንብ ይደግፈን ነበር። እርግጥ ህዝቡ ከማንኛውም ቡድን ጋር ብንጫወት ይደግፈን ነበር። ከግብፅ ጋር ሲሆን ደግሞ ያለውን ነገር ማሰብ ነው። ይህንን ተከትሎ ጨዋታዉን በሜዳችን ብናደርግ የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለው። የሆነው ሆኖ ባሉ ችግሮች ከሜዳችን ውጪ ነው የምንጫወተው። እንደዛም ሆኖ ሦስት ነጥብ ለማሳካት ነው ሀሳባችን። ከጨዋታዎቹ ከተቻለ ስድስት ነጥብ ቢያንስ ደግሞ አራት ነጥብ ይዘን ለመምጣት ነው የምናስበው። ዓላማችን ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ ነው። በስምንት እና በአስራ ምናምን ዓመት መሳተፍ ሳይሆን ይሄ ህዝብ ኳስ ወዳጅ ስለሆነ በየሁለት ዓመቱ ባለው ጊዜ ለመሳተፍ እንሞክራለን።”