ዛሬ 10 ሰዓት ነበልባሎቹ እና ዋልያዎቹ ከሚያደርጉት ጨዋታ በፊት የባለሜዳዎቹ አሠልጣኝ እና አምበል የቅድመ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።
የአይቮሪኮስት የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ካለንበት ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ እየተደረጉ የሚገኝ ሲሆን ዋልያዎቹ የሚገኙበት ምድብ አራትም ዛሬ ከሰዓት ጉዞውን ይጀምራል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከማላዊ ጋር ዛሬ ወሳኝ ጨዋታውን ከማድረጉ በፊት በአሠልጣኙ ውበቱ አባተ እና አምበሉ ሽመልስ በቀለ አማካኝነይ የተሰጠውን የቅድመ ጨዋታ አስተያየት ትናንት ምሽት ያቀረብን ሲሆን የማላዊ አቻቸውም ከብዙሃን መገናኛ አባላት ጋር ያደረጉትን ቆይታ አሁን ይዘን ቀርበናል።
በካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከተካፈሉ በኋላ አሁንም በተከታታይ በመድረኩ ለመቅረብ ሀሳብ ያላቸውን ማላዊዎች የሚያሰለጥኑት ሩሜኒያዊው አሠልጣኝ ማሪዮ ማሪኒካ በስብስባቸው እምነት እንዳላቸው ከመግለፃቸው በፊት ማሸነፍን ብቻ ከማሰብ ጋር ተያይዞ የሚኖር መጠበቅ ጫና እንዳይፈጥር አስረድተው ንግግራቸውን ጀምረዋል። “እኔ ሁል ጊዜ እንደምለው ከነገሮች ብዙ አልጠብቅም። በህይወት ብዙ መጠበቅ ካለ ህይወት ተስፋ አስቆራጭ ነው የሚሆነው። ሁላችንም ህልም እና ተስፋ አለን። ለማሸነፍ የጨዋታ እቅዳችንን ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጅተናል።”
በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑን የያዙት አሠልጣኝ ስብስቡን ከምድብ አሳልፈው 16’ቱ ውስጥ እንዳስገቡት ይታወቃል። አሁን ደግሞ ጠንካራ ከሚመስለው ምድብ ቡድኑን ወደ አህጉራዊ ውድድር ማሳለፍ ተቀዳሚ ዓላማቸው አድርገው ሥራቸውን እየከወኑ ይገኛል። አሠልጣኙ ከዝግጅት ጊዜ ጋር ተያይዞ ያላቸውን ሀሳብ በማስረዳት ስለስብስቡ አስተያየታቸውን ይቀጥላሉ።
“የካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ጊዜ የነበረው የዝግጅት ጊዜ ከዚህ የተለየ ነበር። በሀገራችን ቺዌምቤ ላይ ዝግጅት ማድረግ ጀምረን ነበር። ከሀገር ወጥተንም ሳውዲ አረቢያ ላይ ዝግጅት አድርገን ነበር። በመጨረሻም እዛው ውድድሩ የሚደረግበት ካሜሩን ላይ ዝግጅታችን ቀጥለን ነበር። በአጠቃላይ ለውድድሩ 57 ቀናት አብረን ሆነን ተዘጋጅተን ነበር። አሁን ግን ከዚህ የተለየ ነው። ለጥቂት ቀናት ነው ዝግጅታችንን ያደረግነው። ለጨዋታ መዘጋጀት እና ለውድድር መዘጋጀት ይለያያሉ።
“ከስብስቡ ጥሩ ነገር እንደማገኝ እርግጠኛ ነኝ። እርግጥ አንዳንድ ተጫዋቾች ያጡት ነገር (በተለይ ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የጨዋታ እድል እምብዛም አላገኙም) አለ። ግን እኔ የምሳበው በተጫዋቾቼ ጠንካራ ጎን ነው እንጂ ደካማ ጎን አይደለም። አሁን የመረጥናቸው ተጫዋቾች ደግሞ በዚህ ሰዓት ብሔራዊ ቡድኑን ለማገልገል ብቁ ናቸው። ስለዚህ ተጫዋቾቹ የተመረጡት በጠንካራ ብቃታቸው እንጂ በደካማ ጎናቸው አይደለም።”
አሠልጣኙ ሀሳባቸውን ከማገባደዳቸው በፊት ቡድኑ ሲከተል ከነበረው ‘ኳስን መሰረት’ ካደረገ አጨዋወት ወጥቶ ቀጥተኝነት እየተከተለ ስለመምጣቱ ተጠይቀው የበፊቱ አጨዋወት ውጤታማ አለመሆኑን ተከትሎ ለውጡ እንደመጣ የሚገልፅ ይዘት ያለው ምላሽ ሰጥተዋል።
“በትክክል ካስታወስኩ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከካሜሩን ጋር ስንጫወት በጣም ብዙ የኳስ ቅብብሎች ነበሩን። በጨዋታው 410 ጊዜ ኳስ ተቀባብለናል ነገርግን አንድም ጊዜ ተጋጣሚ ግብ ክልል ተጠግተን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አላደረግንም። ቡድኑ ነጥብ እና ውጤት ያስፈልገዋል። ሁሉም ነገር የሚደረገው እንዳለን የተጫዋች ስብስብ እና እንደምንገጥመው ተጋጣሚ ነው። ስለዚህ ያለንን ነገር ታሳቢ በማድረግ እና የምንገጥመውን ቡድን በማገናዘብ ነው ለመጫወት የምንሞክረው።”
በመጨረሻም የቡድኑ አምበል ጆን ባንዳ ተጫዋቾቹ ለዛሬው ፍልሚያ እንደተዘጋጁ ሲናገር ተደምጧል። “በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ አለብን። ሁሉም ተጫዋቾች በልምምድ ላይ በደንብ ነው የሰሩት። አሠልጣኙን ማንን ነው የምታሰልፈው ብለህ ብትጠይቀው የራስ ምታት እንደያዘው ይነግርሀል። ነገ ምንም ሰበብ አይኖረንም።”
ከጨዋታው ጋር በተያያዘ ዜና 10 ሰዓት ላይ በቢንጉ ስታዲየም የሚደረገውን ጨዋታ ደጋፊዎች እንዲከታተሉ የተዘጋጀው የስታዲየም መግቢያ ትኬት ሙሉ ለሙሉ ተሸጦ ማለቁ ከሰዓታት በፊት ይፋ ሆኗል።