መሐመድ ሳላ ከኢትዮጵያው ጨዋታ ውጪ ሆኗል

የፊታችን ሐሙስ ከዋልያዎቹ ጋር ፍልሚያ የሚጠብቃት ግብፅ መሐመድ ሳላ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሆኖባታል።

የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ካሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ የአህጉራችን ሀገራት እየተከናወኑ የሚገኝ ሲሆን በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በትናንትናው ዕለት የማጣሪያውን የመጀመሪያ ጨዋታ አድርጎ በማላዊ ተረቷል። ሁለተኛ ጨዋታውንም ከግብፅ ጋር እዛው ማላዊ ሊሎንግዌ ላይ ከሦስት ቀናት በኋላ ያከናውናል።

በዚሁ ምድብ ትናንት ምሽት ጊኒን በሜዳዋ ያስተናገደችው ግብፅ አንድ ለምንም ያሸነፈች ሲሆን ለሀሙሱ ጨዋታ ደግሞ ነገ ቀትር ወደ ማላዊ ጉዞዋን የምታደርግ ይሆናል። በግብፅ ተነባቢ በሆነው ድረ-ገፅ ያላኮራ የሚፅፈው ሀዲ ኤል-ማዳኒ ከብሔራዊ ቡድኑ አገኘሁት ብሎ ለዝግጅት ክፍላችን አሁን በላከው መረጃ መሠረት ደግሞ ፈረኦኖቹ ወሳኙ ተጫዋቻቸው መሐመድ ሳላን ከሐሙሱ ጨዋታ ውጪ ማድረጋቸውን ያመላክታል።

ጋዜጠኛው እንደገለፀልን ከሆነ ተጫዋቹ ከትናንቱ ጨዋታ በኋላ የኤክስ ሬ ምርመራ ተደርጎለት ጡንቻው ላይ ጉዳት በማስተናገዱ የሐሙሱ ጨዋታ እንዲያልፈው እና እረፍት እንዲያደርግ ተወስኗል። ከሳላ በተጨማሪ ከአራት ቀናት በፊት የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶበት ከስብስቡ የተገለለው ኤል-ሼናዊም ከቫይረሱ ባለማገገሙ ነገ ወደ ማላዊ እንደማያቀና ሲገለፅ ትሬዜጌትም (መሐሙድ አህሙድ ኢብራሂም ሀሰን) መጠነኛ ጉዳት ላይ በመሆኑ ጨዋታው ላይ መሰለፉ አጠራጣሪ ሆኗል።

ያጋሩ