በሴካፋ ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የምድቡ ሁለተኛ ሆኖ ወደ ግማሽ ፍፃሜው አልፏል።
በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ስምንት ብሔራዊ ቡድኖችን ተሳታፊ በማድረግ ካሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ እየተከናወነ የሚገኘው የሴቶች የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ትናንት እና ዛሬ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎቹን አከናውኖ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፉ 4 ቡድኖችን ለይቷል።
በምድብ አንድ አስተናጋጇ ዩጋንዳን ጨምሮ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ እና ጂቡቲ ሦስት ሦስት ጨዋታዎችን አድርገው ዩጋንዳ በ9 ቡሩንዲ ደግሞ በ6 ነጥቦች አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸው መረጋገጡ ይታወቃል።
በምድብ ሁለት ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ዛንዚባር ተደልድለው የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የምድብ የመጨረሻ ጨዋታቸውን በእኩል ሰዓት አከናውነዋል። በቡጌምቤ ስታዲየም ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ የጠበበ ተስፋ ይዛ ወደ ሜዳ የገባችው ደቡብ ሱዳንን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአረጋሽ ካልሳ ሦስት እንዲሁም በሎዛ አበራ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል አራት ለምንም አሸንፏል።
በዚሁ ምድብ ዛንዚባርን የገጠመችው ታንዛኒያ ደግሞ ደርዘን (12) ግቦችን በማዝነብ አሸንፋለች። ውጤቱን ተከትሎም ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ ጋር እኩል 7 ነጥቦችን ብታገኝም በግብ ክፍያ ልቃ ምድቡን በበላይነት አጠናቃለች። ሉሲዎቹም ታንዛኒያን ተከትለው ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
በግማሽ ፍፃሜው የምድብ አንድ መሪ ሆና ያጠናቀቀችው የውድድሩ አስተናጋጅ ዩጋንዳ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሀሙስ 7 ሰዓት ስትጫወት ታንዛኒያ ደግሞ ቡሩንዲን በተመሳሳይ ቀን 10 ሰዓት ላይ ገጥማ አሸናፊዎቹ ለፍፃሜ የሚፋለሙ ይሆናል።