ግብፅ ተጨማሪ ተጫዋች ከሐሙሱ ጨዋታ ውጪ ሆኖባታል

ከነገ በስትያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የምትገጥመው ግብፅ በጉንፋን ህመም ምክንያት ተከላካዩዋን አጥታለች።

በቀጣዩ ዓመት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር አይቮሪኮስት በሚዘጋጀው የአህጉሩ ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ሀገራት በ12 ምድቦች ተከፋፍለው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያከናወኑ የሚገኝ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ከነገ በስትያ ለማድረግ እየተሰናዳ ይገኛል።

ይህንን ዘገባ በምንሰራበት ሰዓት ልምምዱን እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ አሳሳቢ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን ሱራፌል ዳኛቸው እና ያሬድ ባየህ ብቻ በትናንቱ የልምምድ መርሐ-ግብር መጠነኛ ሥራ ብቻ እንዲሰሩ መደረጉን አውቀናል። ይህም የሆነው ተጫዋቾቹ ከደረሰባቸው መጠነኛ ጉዳት ቶሎ እንዲያገግሙ ታስቦ እንደሆነ እና ጉዳታቸው ከጨዋታው ውጪ እንደማያደርጋቸው ተጠቁሟል።

በተጋጣሚው ግብፅ በኩል ያሉ መረጃዎችን ያላኮራ ድረ-ገፅ ላይ ከሚሰራው ሀዲ ኤል-ማዳኒ እያገኘን ወደ እናንተ እያደረስን መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም መሐመድ ሳላ (በጉዳት) እና ኤል-ሼናዊ (በኮሮና ቫይረስ) ከሀሙሱ ጨዋታ ውጪ መሆናቸውን እንዲሁም ትሬዝጌት ደግሞ መሰለፉ አጠራጣሪ እንደሆነ አስነብበን ነበር።

ጋዜጠኛው አሁን በላከልን መረጃ መሠረት ደግሞ የመሐል ተከላካዩ ያስር ኢብራሂም በጉንፋን ህመም ምክንያት ወደ ማላዊ ካቀናው ስብስቡ ውጪ ሆኗል።

1 ሜትር ከ85 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው እና በሀገሪቱ ከሚገኙ ታላላቅ ክለቦች መካከል አንዱ ለሆነው አል-አህሊ የሚጫወተው ያስር ኢብራሂም ከጊኒ ጋር በተደረገው የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ 90 ደቂቃዎችን ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ ህመሙ እንዳጋጠመው ተመላክቷል። ከዚህም መነሻነት ስብስቡን ለቆ ወደ ክለቡ እንዲመለስ ተደርጓል።

በተያያዘ ዜና ከደቂቃዎች በፊት በግል በረራ የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ወደ ማላዊ ጉዞ እንደጀመሩ ታውቋል።