የዋልያዎቹ አሠልጣኝ እና አምበል ከወሳኙ ጨዋታ በፊት ሀሳብ ሰጥተዋል

👉”የሳላ መኖር እና አለመኖር የእኛ እቅድ ላይ ምንም ተፅዕኖ አያደርግም” ውበቱ አባተ

👉”ከምድባችን ለማለፍ በምናደርገው ጉዞ የነገው ጨዋታ ወሳኝ ነው” ውበቱ አባተ

👉”እኔም ሆነ ጓደኞቼ የትኛውንም ቡድን አግዝፈን አናይም” ሽመልስ በቀለ

በቀጣዩ ዓመት በሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ 4 ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ በማላዊ አቻው በአንድ ግብ ልዩነት የተረታው ቡድኑ በነገው ዕለት ከግብፅ አቻው ጋር ሁለተኛ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል። ከጨዋታው በፊት ደግሞ የዋልያዎቹ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ ሽመልስ በቀለ ከብዙሃን መገናኛ አባላት ጋር ተከታዩን የቅድመ ጨዋታ ቆይታ እድርገዋል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ

በጨዋታው መሐመድ ሳላ አለመኖሩ የሚፈጥረው ነገር አለ?

ይሄንን ዜና ትናንት ነው የሰማነው። በእግር ኳስ ያጋጥማል። ጉዳቶች እና የተለያዩ ነገሮች ይፈጠራሉ። እኛ ግን እርሱ የለም ብለን የምንቀይረው ነገር ምንም የለም። እሱ ኖረም አልኖረ ወደ ሜዳ የምንገባው ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው። የሳላ መኖር እና አለመኖር የእኛ እቅድ ላይ ምንም ተፅዕኖ አያደርግም።

ሳላ ትልቅ ተጫዋች ነው። እሱ ሲጫወት እና ሳይጫወት የሚኖሩ ጥቅም እና ጉዳቶች አሉ። ይህ ቢሆንም ግብፅ ብዙ ጥሩ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች ያሏት ቡድን ናት። ይህ ጨዋታውን አይቀይረውም።

ከማላዊ ሽንፈት በኋላ የነገው ጨዋታ ምን ያህል ወሳኝ ነው?

ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ጨዋታዎችን ማሸነፍ አለብን። በመጀመሪያው ጨዋታ ጥሩ ብንጫወትም በማላዊ ተሸንፈናል። ከምድባችን ለማለፍ በምናደርገው ጉዞ የነገው ጨዋታ ወሳኝ ነው።

በቡድኑ ውስጥ የጉዳት ዜና አለ?

በቡድናችን ውስጥ አንድ ተጫዋች ተጎድቷል። ሱራፌል ዳኛቸው ጨዋታውን ለማድረግ ብቁ አይደለም። ልምምዶችን እየጨረሰ አይገኝም። ምናልባት እሱ ጨዋታው ሊያመልጠው ይችላል። ከእሱ ውጪ ግን ሁሉም ተጫዋቾች ጨዋታውን ለማድረግ ዝግጁ ናቸው።

በጨዋታው ሊኖራቸው ስለሚችል አቀራረብ…?

እንደሚታወቀው ግብፅ በአፍሪካ እግር ኳስ ጥሩ ታሪክ አላት። በመጨረሻው የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚ ነበረች። በቡድኗ ውስጥም ጥሩ ብቃት እና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች አሉ። የምትጫወትበትም መንገድ በጣም ጥሩ ነው። እኛም በተመሳሳይ መንገድ ነው የምንጫወተው። ግን ጥሩ መጫወት ብቻ ሳይሆን ውጤቱም ያስፈልገናል። በአጠቃላይ ለሁለታችንም ጥሩ ጨዋታ እንደሚሆን አስባለው። ነጥብ በማግኘት ረገድ ግን በደንብ መፋለም አለብን። ከመጀመሪያው ጨዋታም ተሽለን መቅረብ አለብን።

በማላዊው ጨዋታ የተሻለ ኳስ ተቆጣጥረው ተጫውተው ሁለት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ ስለማድረጋቸው….?

በማላዊው ጨዋታ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር እና ወደ ላይ ተጠግተን ተጋጣሚ ላይ ጫና ለማሳደር በመሞከር ለመጫወት ሞክረናል። በዚህም የተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ ላይ ደርሰን ነበር። የተወሰኑ የግብ ማግባት ሙከራዎችንም ለመፍጠር ሞክረናል። ግን ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ማግኘት አልቻልንም። ማላዊ ሁለት ካገባች በኋላ ወደ ኋላ ማፈግፈግ ነበር የመረጠችው። የነገው ጨዋታ ግን ይለያል። ከግብፅ ጋር 0ለ0 ሆነን ነው የምንጀምረው። ግን የሚፈጠሩት አጋጣሚዎች ጨዋታውን ይወስኑታል። ግን እኛ በመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ ኳሊቲያችንን መጨመር አለብን።

ሽመልስ በቀለ

ግብፅ ስለመጫወቱ እና ስለ ተጫዋቾች ዝግጁነት…?

ጨዋታው የተለየ ነገር የለውም። ረጅም ዓመት ግብፅ ብጫወትም እኔም ሆነ ጓደኞቼ የትኛውንም ቡድን አግዝፈን አናይም። ከባለፈው ስህተታችን በጣም ተምረን የነገውን ጨዋታ በጥሩ ውጤት ለመወጣት እንሞክራለን ብዬ አስባለው። አሠልጣኞቻችን ጥሩ እንደመሆናቸውም መጠን መጫወት እንደምንችል በቪዲዮ እና የተለያዩ መንገዶች ስለመለሱን የነገውን ጨዋታ በጥሩ ውጤን እንወጣለን ብዬ አስባለው።

ያጋሩ