👉”የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጣም ጥሩ ቡድን ነው” ኢሀብ ጋላል
👉”ያጣናቸው ተጫዋቾች በጣም ጥሩ ተጫዋቾች ናቸው። ግን ሌሎች ብዙ በጣም ጥሩ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች በስብስባችን ይገኛሉ” ኢሀብ ጋላል
👉”ሁለተኛ ጨዋታችንን አሸንፈን የምድባችን የበላይ ሆኖ ለመቀጠል ተዘጋጅተናል” አምር ኤል ሶላያ
ነገ ምሽት 1 ሰዓት የኢትዮጵያ እና ግብፅ ብሔራዊ ቡድኖች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታቸውን በቢንጉ ስታዲየም ያከናውናሉ። ከጨዋታው በፊት የሁለቱም ቡድን አሠልጣኝ እና አምበሎች ረፋድ ላይ ከብዙሃን መገናኛ አባላት ጋር ቆይታ ያደረጉ ሲሆን በቅድሚያም የአሠልጣኝ ውበቱ እና አምበሉ ሽመልስን ንግግር ይዘን ቀርበን ነበር። አሁን ደግሞ የተጋጣሚያችን ግብፅ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኢሀብ ጋላል እና አምበሉ አምር ኤል ሶላያ የሰጡትን አጠር ያለ መግለጫ እንደሚከተለው እናቀርበዋለን።
አሠልጣኝ ኢሀብ ጋላል
ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ስለዝግጅታቸው…?
በመጀመሪያ ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማለት የምፈልገው ነገር አለኝ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሁን በጣም ጥሩ ቡድን ነው። ጥሩ የተዘጋጀ ቡድን ነው። በተለይ ከአራት ወራት በፊት በአፍሪካ ዋንጫው ያሳዩት ብቃት ጥሩ ነበር። በቡድኑ በኩል አንዳንድ ተጫዋቾችን እናውቃለን። አምበሉም እኛው ጋር ግብፅ እየተጫወተ እንደሚገኝ እናውቃለን። በአጠቃላይ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አሉዋቸው። ዝግጅታችንን በተመለከተ ለነገው ጨዋታ ጥሩ ተዘጋጅተናል።
መሐመድ ሳላን ጨምሮ በጉዳት የማይሰለፉት ተጫዋቾች ክፍተት ይፈጥሩ ይሆን….?
ያጣናቸው ተጫዋቾች በጣም ጥሩ ተጫዋቾች ናቸው። ግን ሌሎች ብዙ በጣም ጥሩ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች በስብስባችን ይገኛሉ። ያለ እነርሱ ለመጫወት ተዘጋጅተናል። እንዳልኩት ያጣናቸው ትልቅ ተጫዋቾች ቢሆኑም ሌሎቹ ጥሩ ተጫዋቾቻችን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
የነገው ጨዋታ ወሳኝነት…?
ነገ እንዲሁም ከማላዊ ጋር በደርሶ መልስ የሚደረጉት ጨዋታዎች የትኛው ቡድን ቀድሞ ወደ አፍሪካ ዋንጫው እንደሚያልፍ ምልክት የሚሰጡ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ከሜዳው ውጪ በገለልተኛ ሜዳ መግጠም…?
ጥቅም አለው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የራሱን ጨዋታ ከሜዳው ውጪ መጫወቱ ቀላል አይደለም። አሁን የምንጫወትበት ሜዳ ጥሩ እንደሆነ አስባለው። ግን በሀገራችሁ መጫወት ደግሞ የተለየ ነው። በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ጋር የሚጫወት የትኛውም ቡድን ከሜዳው ውጪ ቡድኑን መግጠሙ ትልቅ ጥቅም ይሰጠዋል።
አምበሉ አምር ኤል ሶላያ
ስለ ጨዋታው…?
በአሁኑ ሰዓት ቀላል የሚባል ጨዋታ የለም። እኛ ሁሉንም ጨዋታዎች የምንቀርበው ለማሸነፍ ነው። በአጠቃላይ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታችንን አሸንፈን የምድባችን የበላይ ሆኖ ለመቀጠል ሁላችንም ተጫዋቾች ተዘጋጅተናል።