የነገው ጨዋታ በግብፃዊው አንደበት…

ነገ ምሽት 1 ሰዓት ላይ ከሚደረገው የዋልያዎቹ እና ፈረኦኖቹ ጨዋታ በፊት በግብፅ ተነባቢ በሆነው ድረ-ገፅ ያላኮራ ከሚፅፈው ጋዜጠኛ ሀዲ-ኤልማዳኒ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ !

ቀጣዩ የአህጉራችን ትልቁ የሀገራት ውድድር በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር አይቮሪኮስት እንደሚዘጋጅ ይታወቃል። በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ደግሞ 48 ሀገራት በ12 ምድቦች ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ ጀምረዋል። በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በምድብ 4 ከግብፅ ፣ ጊኒ እና ማላዊ ጋር ተደልድሎ ይገኛል። ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከማላዊ ጋር ያከናወነው ቡድኑ ሁለት ለአንድ ተረቶ ከግብፅ ጋር የሚደረገውን የነገ ሁለተኛ ጨዋታ እየተጠባበቀ ይገኛል።

የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ከነበሩ ሦስት ሀገራት መካከል የሚገኙት ኢትዮጵያ እና ግብፅ ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና የቀደመ እግር ኳሳዊ ተቀናቃኝነት ያላቸው ሀገራት ናቸው። ነገ ምሽት 1 ሰዓት ከ25 ዓመታት በኋላ እርስ በእርስ የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በመካከላቸው ሰፋ ያለ ልዩነት ቢኖርም ሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ያሉት ነገሮች ጨዋታቸውን እንዲጠበቅ አድርገውታል። ከወሳኙ ጨዋታ አስቀድሞ ስለሁለቱም ቡድኖች አዳዲስ መረጃዎችን ስናደርስ የነበረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከተጋጣሚያችን ግብፅ በኩል የሚገኙ መረጃዎችን ሲያደርሰን ከነበረው ጋዜጠኛ ጋር ደግሞ ስለነገው ጨዋታ አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል።

በግብፅ እግር ኳስ ላይ ብቻ ትኩረታቸውን አድርገው ከሚሰሩ ድረ-ገፆች መካከል አንዱ በሆነው ያላኮራ የሚሰራው ሀዲ-ኤልማዳኒ ለቡድኑ ቅርብ የሆነ ጋዜጠኛ እንደመሆኑ ከጨዋታው በፊት መነሳት አለባቸው ብለን ያሰብናቸውን ጥያቄዎች አድርሰነው ምላሽ ሰጥቶናል። ከ2016 ጀምሮ ለድረ-ገፁ የሚፅፈው ሀዲ ኢትዮጵያዊያንን ሰላምታ እንድናደርስለት አደራ ካለ በኋላ ለጠየቅነው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ይዟል። ከጋዜጠኛው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ !

የነገውን ጨዋታ ለማድረግ ቡድኑ ምን ያህል ተዘጋጅቷል ?

“በምድቡ ታላላቅ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በአዲሱ አሠልጣኛችን ስር ገና አንድ ጨዋታ ነው ያደረግነው። ነገ ቡድኑ በአዲሱ አሠልጣኙ ስር ሁለተኛ ጨዋታውን ነው የሚያደርገው። የሆነው ሆኖ አንዳንድ ክፍተቶች ቢኖሩም ዝግጅታችን ጥሩ ነው። በተለይ ከጉዳት ጋር ተያይዞ መጠነኛ ክፍተቶች አሉ። ነገር ግን ቡድኑ የነገውን ጨዋታ ለማድረግ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

ግብፃዊያን ከነገው ጨዋታ ምን ይጠብቃሉ ?

“እውነት ለመናገር ግብፃዊያን በብሔራዊ ቡድኑ ወቅታዊ ብቃት ደስተኛ አይደሉም። በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታም ደጋፊዎች ስታዲየሙን ሞልተውት አልነበረም። ይህ ቢሆንም ግን ከነገው ጨዋታ ጥሩ ነገር ይጠብቃሉ። ቢያንስ ቢያንስ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ቡድኑ ማግኘት አለበት። ሽንፈት ከተመዘገበ ግን ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ነው የሚነሳው። በተለይ አሠልጣኙ ላይ ጫናዎች መበርታታቸው የማይቀር ነው።

ቡድኑ መሐመድ ሳላን ማጣቱ ምን ያህል ይጎዳዋል ?

“ሳላ አለመኖሩ ቡድኑን ይጎዳዋል። ሊቨርፑል ሳላ ሲጎዳ ተጫዋቹን እንደሚያጣው የግብፅ ብሔራዊ ቡድንም ሳላ ባለመኖሩ የሚጎዳው ነገር አለ። ግን ሌሎቹ የቡድኑ ተጫዋቾች የሚፈለገውን ውጤት ያመጣሉ ብዬ አስባለው።

ከሳላ ውጪ ያሉት ጉዳቶችስ ? ጉዳቶች መበርከታቸው የሚፈጥረው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው ?

“ልክ ነው ጉዳቶች በርክተዋል። ካሉት ጉዳቶች ቡድኑ ላይ መሳሳት የሚያመጣው ቦታ ደግሞ የኋላ መስመሩ ላይ ይመስለኛል። ያስር ኢብራሂም በጉንፋን ህመም ምክንያት ከቡድኑ ጋር አይገኝም። የእርሱ አለመኖር የተወሰነ መሳሳት በኋላው መስመር ላይ የሚያመጣ ይመስለኛል።

በግብፅ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ተቃርኖ ጨዋታው ላይ የሚፈጥረው ነገር አለ ?

“እስካሁን በግብፅ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው የፖለቲካ ልዩነት እግር ኳሱ ውስጥ አለመኖሩ ደስታ ሰጥቶኛል። ግን የነገው ጨዋታ በወጣለት መርሐ-ግብር መሰረት ኢትዮጵያ ላይ ቢደረግ ኖሮ ለግብፅ በጣም ከባድ ነበር። ፈተናውን የሚያመጣው ያለው የፖለቲካ ነገር ሳይሆን የአየር ፀባዩ ነው። ጨዋታው በገለልተኛ ሜዳ መደረጉ ለግብፅ ጥሩ ነው። ግን ፖለቲካው እግር ኳሱ ውስጥ ባለመግባቱ በጣም ደስተኛ ነኝ።

የግብፅ ብሔራዊ ቡድን በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ያሳየው ብቃት ምን ይመስላል ?

“የጊኒው ጨዋታ ለብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ኢሀብ ጋላል የመጀመሪያው ይፋዊ ጨዋታ ነበር። እርግጥ ከዛም በፊት ምንም የወዳጅነት ጨዋታም አላደረገም። በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች በጉዳት ያጣቸው ተጫዋቾች አሉ። በተለይ በአማካይ መስመሩ ላይ ትሬዝጌት በሚያሟሙቅበት ሰዓት ኤል ኔኒ ደግሞ በልምምድ ላይ ተጎድተው ምርጫውን ለመከለስ ተገዷል። ዞሮ ዞሮ በመጀመሪያው ጨዋታ ጊኒን አሸንፈናል። ግን በእንቅስቃሴ ረገድ ቡድኑ አመርቂ አልነበረም። ብዙ ሰዎችም አሠልጣኙን ሲተቹት ነበር። የነገው ጨዋታ ደግሞ ከሜዳ ውጪ የሚደረግ ስለሆነ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።

የቡድኑ የጨዋታ መንገድ ምን ይመስላል ?

“አሠልጣኙ ማጥቃት የሚወድ እንደሆነ ይታወቃል። ነገር ግን ከጊኒ ጋር በነበረው ጨዋታ ይህንን ማየት አልቻልንም። ግን ደግሞ አሠልጣኙ ተጫዋቾቹን ማወቂያ ጊዜ ያስፈልገዋል። ምናልባት 5 እና 6 ጨዋታዎች ያስፈልጉት ይሆናል። በደንብ ተጫዋቾቹን ካወቀ በኋላ ግን ሊፈረጅ ይገባል። አሁን ግን አሠልጣኙ አለው ተብሎ የሚታሰበው የጨዋታ መንገድ በጊኒው ጨዋታ አልታየም።

የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ማነው ?

“ምናልባት የአል አህሊው ዚዙ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ነው ማለት እችላለሁ። ትሬዜጌም ስለመጫወቱ እርግጠኛ ባልሆንም ጥሩ ተጫዋች ነው። ለጋላታሳራይ የሚጫወተው አጥቂው ሙስጠፋ መሐመድ ፣ መሀመድ ሻናዊ (ከኮቪድ መመለሱ እርግጥ ባይሆንም) ፣ በተጨማሪም አቡጋባልም ጥሩ ግብ ጠባቂ ነው። በጥቅሉ ብዙ ጥሩ ተጫዋቾች አሉን ፤ ምንም የማይወጣለት ግን መሀመድ ሳላ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በግብፃዊያን ዘንድ ምን አይነት ምስል አለው ?

“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ታሪካዊ ቡድን ነው። እንደሱዳን ሁሉ ከግብፅ ጋር የአፍሪካ ዋንጫን የመሰረተች ሀገር ብትሆንም በትልቅ ደረጃ ተፎካካሪ አይደለችም። አላውቅም ለምን እንደ ኢትዮጵያ ያለ ትልቅ ሀገር ትልቅ ብሔራዊ ቡድን እንደሌለው። በግብፅ ሊግ አንዳንድ ተጫዋቾችን እናያለን። ኢትዮጵያዊ መንፈስ ይታይባቸዋል። ቀስ በቀስ ግን ብቃታቸው ይደበዝዛል። በእርግጥ እንደ ሽመልስ በቀለ ዓይነት ተጫዋች ለሌሎች ጥሩ ማሳያ ነው። ሳላዲን ሰዒድም እንዲሁ ጥሩ ተጫዋች እንደነበር አስታውሳለሁ።

ኢትዮጵያን ሜዳዋ ላይ አለመግጠም ምን ዓይነት ጥቅም አለው ?

“ትልቅ ጥቅም አለው ! ምክንያቱም በኢትዮጵያ ከባህር ጠለል በላይ ያለው ከፍታ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ጨዋታው ከኢትዮጵያ ውጪ መሆኑ የግብፅ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ጨዋታውን በምቾት እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። ለኢትዮጵያውያን እና ለኬንያዊያን በሜዳቸው ላይ መጫወት ትልቅ ጥቅም አለው። ስለዚህ ጨዋታው ማላዊ ላይ መደረጉ ለግብፅ ትልቅ ጥቅም አለው።

ጨዋታው ትኩረት እንዲስብ የሚያደርገው ምክንያት ምንድን ነው ?

“ጨዋታውን ልዩ የሚያደርገው ከሰባ ዓመት በላይ የሚሆነውን ይህን የካፍ ውድድር የመሰረቱ ሀገራት መሆናቸው ነው። ኢትዮጵያ ግን ከፍ ወዳለው ደረጃ መመለስ ይኖርባታል። በየአምስት እና ስድስት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ጣልቃ ብቻ የምትሳተፍ ሀገር መሆን የለባትም። በውድድሩ ያላትን ታሪክ የሚመጥን ትልቅ ቡድን ሊኖራት ይገባል።”