ሠራተኞቹ ወደ ልምምድ ተመልሰዋል

ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ልምምምድ ሳይጀምሩ ቀርተው የነበሩት የወልቂጤ ተጫዋቾች ዛሬ ተሰባስበው ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።

በአሠልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው ወልቂጤ ከተማ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከተቋረጠ በኋላ ለተጫዋቾቹ እረፍት ሰጥቶ ከ12 ቀናት በፊት ልምምዱን ለመጀመር አስቦ የነበረ ቢሆንም ከደሞዝ ጋር በተያያዘ የቡድኑ አባላት ልምምድ ሳይጀምሩ ቀርተው እንደነበር መዘገባችን ይታወቃል። አሁን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ደግሞ ተጫዋቾቹ ያቀረቡት ጥያቄ በከፊል ምላሽ በማግኘቱ ወደ ልምምድ መመለሳቸውን ይጠቁማል።

የሦስት ወር ደሞዝ እንዳልተፈፀመላቸው በመግለፅ ልምምድ ያልጀመሩት ተጫዋቾቹ የከተማው እና የዞኑ አስተዳደር በጋራ በመሆን ጥያቄያቸው ለመፍታት ባደረጉት ጥረት የሁለት ወር ደሞዛቸውን ማግኘታቸውን አውቀናል። ይህንን ተከትሎም የብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ላይ ከሚገኘው ረመዳን የሱፍ፣ ጉዳት ላይ ከሚገኘው አበባው ቡጣቆ እንዲሁም ቅጣት ላይ በመሆኑ እረፍት ከተሰጠው ጌታነህ ከበደ ውጪ የሚገኙት ተጫዋቾች ባህር ዳር አሲኖሀራ ሆቴል ገብተዋል። አመሻሽ ከ10:30 ጀምሮም ልምምዳቸውን እንደሰሩ ለማወቅ ችለናል።

ሊጉ የፊታችን ማክሰኞ ከእረፍት መልስ ሲመለስ ወልቂጤ ከተማ ከ መከላከያ ጋር የ26ኛ ሳምንት ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

ያጋሩ