በሴቶች የሴካፋ ዋንጫ ኢትዮጵያ ታንዛኒያን 2ለ1 በመርታት የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች፡፡
የሉሲዎቹ አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል በ4-3-3 የተጫዋች አደራደር ቅርፅ በዩጋንዳ 1ለ0 ከተረቱበት ቋሚ አሰላለፍ ረድኤት አስረሳኸኝን ወደ ተጠባባቂ በማውረድ በምትኩ ቱሪስት ለማን በቀዳሚው አሰላለፍ ተጠቅመዋል፡፡ በምድብ ጨዋታ ተገናኝተው 2ለ2 በሆነ ውጤት ተለያይተው የነበሩት ታንዛኒያ እና ኢትዮጵያ በዛሬው ጨዋታቸው የመጀመሪያው አጋማሽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፍ ያለ የሜዳ ላይ ንቃት በርትቶ የታየበት ነበር፡፡ በተለይ ወደ ግራ መስመር በማድላት ከብዙዓየሁ ታደሰ እና አረጋሽ ካልሳ መነሻቸውን ካደረጉ ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር ከጅምሩ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ በቀዳሚነትም 9ኛው ደቂቃ ላይ በታንዛኒያ የግራ መስመር አረጋሽ ካልሳ የግል አቅሟን ተጠቅማ የሰጠቻትን ኳስ በግራ እግሯ መትታ ተከላካዩዋ ብዙዓየሁ ታደሠ ወደ ጎልነት በመለወጥ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡
የኢትዮጵያን የኳስ ቅብብል ስህተት እየጠበቁ ከርቀት ሙከራን በማድረግ ግብ ለማግኘት ታንዛኒያዎች ዋነኛ የጨዋታ መንገዳቸው ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በተለይ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነችሁ የታንዛኒያ እና የሲምባ ኪዊንሷ አጥቂ ኦፓ ክሌመንት በተደጋጋሚ የሉሲዎቹን የተከላካይ ስህተት ለመጠቀም ትጋት ቢታይባትም ከተከላካዮቹ ልቃ ልዩነት ለመፍጠር ግን አልቻለችም፡፡
ኳስን መሠረተ ባደረገ ቅብብል በተሻለ አጨዋወት ወደ መስመር አዘንብለው መጫወታቸውን የቀጠሉት የአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ተጫዋቾች 27ኛ ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ኳስ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ መሳይ ተመስገን በታንዛኒያ ተከላካዮች መሀል የሰጠቻትን ኳስ አጥቂዋ ቱሪስት ለማ በአግባቡ በመቆጣጠር ወደ ጎል ለውጣው 2ለ0 ወደ ሆነ ውጤት ቡድኗን አሸጋግራለች፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል ለመድረስ ባይቸገሩም ንፁህ ዕድልን ለማግኘት የተቸገሩት ታንዛኒያዎች 38ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዩዋ ኒካ ካሶንጋ ማዓድን ሳህሉ በአሚና አሊ ላይ ጥፋት መስራቷን ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ከርቀት አክርራ ስትመታ ታሪኳ በርገና ያወጣችባት ብቸኛዋ የቡድኑ ግልፅ ዕድል ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ አጋማሹ ሊገባደድ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩ አረጋሽ ካልሳ ሉሲዎቹ ብልጫ በወሰዱበት የግራ መስመር ላይ ወደ ሳጥን እየገፋች ገብታ ወደ ጎል መትታ ግብ ጠባቂዋ አድናባታለች።
ከእረፍት መልስ የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ሲቀጥል ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር መጠነኛ መቀዛቀዝ የታየበት ሆኗል፡፡ ሉሲዎቹ አብዛኛዎቹን የጨዋታ ደቂቃዎች የኋላ መስመራቸውን በመቆጣጠር ያስቆጠሩት ጎል አስጠብቆ ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ የታየ ሲሆን ታንዛኒያዎች በበኩላቸው የተጫዋች ለውጥ በማድረግ በተሻጋሪ ኳሶች ወደ ጨዋታ ሪትም ለመመለስ ብርቱ ትግል አድርገዋል፡፡ ብዙም የግብ ሙከራን በአጋማሹ መመልከት ባንችልም በአመዛኙ ሀይል የተቀላቀለበትን የጨዋታ ሂደት ዩጋንዳዊቷ የመሀል ዳኛ ዲያና ሙሩንጂ በተደጋጋሚ መፍቀዷ የሁለተኛውን አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በመጠኑም ቢሆን ያደበዘዘ ነበር፡፡ ሉሲዎቹ ከፈጠሩት ሦስት ዕድሎች ቱሪስት ለማ የመረጋጋት ችግር ተስተውሎባት ሁለት ጊዜ ግልፅ የሆነ ዕድልን አግኝታ ያልተጠቀመችበት ይወሳል፡፡
በተለየ መልኩ 76ኛው ደቂቃ አረጋሽ ካልሳ ሰጥታት ቱሪስት መረጋጋት ባለመቻሏ በቀላሉ የተበላሸባት በአንፃራዊነት የተሻለችዋ ነበረች፡፡ 79ኛው ደቂቃ ላይ የብርቄ አማረ የቦታ አጠባበቅ ድክመትን የተመለከተችው የመስመር ተጫዋቿ ማዋና ሀሚስ ወደ ጎል ስትልክ ልማደኛዋ ኦፓ ክሌመንት ወደ ግብነት ለውጣው ታንዛኒያን ወደ ጨዋታ ብትመልስም ጨዋታው ተጨማሪ ጎል ሳያስመለክተን አንድም የተጫዋች ቅያሪ ባላደረጉት ሉሲዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ኢትዮጵያም ውድድሩን ሦስተኛ በመሆን የነሀስ ተሸላሚ መሆኗን ስታረጋግጥ አዘጋጇ ዩጋንዳ እና ብሩንዲ በአሁኑ ሰዓት የፍፃሜ ጨዋታቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ።