ለተከታታይ አስር ቀናት ሲደረግ የነበረው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ በአስተናጋጇ ሀገር ዩጋንዳ ቻምፒዮንነት ተጠናቋል፡፡
በስምንት የቀጠናው ሀገራት መካከል በሁለት ምድብ ተከፍሎ ለአስር ተከታታይ ቀናት ሲደረግ የነበረው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ በአስተናጋጇ ሀገር ዩጋንዳ አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ በምድብ አንድ ላይ ተደልድለው የነበሩትን ዩጋንዳን እና ብሩንዲን ዳግም ያገናኘውን የዛሬውን ጨዋታ ለመታደም የዩጋንዳ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሆን ኢድዋርድ ተከታትለውታል፡፡
ዘጠኝ ሰዓት ሲል ጅምሩን ባደረገው ጨዋታ አዘጋጇ ዩጋንዳ ብሩንዲን 3-1 ረታ ነው ቻምፒዮን መሆን የቻለችው። ሳንድራ ናብዊቲሜ ሁለት ጎሎችን ከመረብ ስታሳርፍ ፣ ፋዚላ ኢኩዋፑት ቀሪዋን የዩጋንዳ ጎል አስቆጣሪ ሆናለች፡፡ የብሩንዲን ብቸኛ ግብ ጄይል ብኩሩ ከመረብ ማሳረፍ ችላለች፡፡ ጨዋታው 3-1 መጠናቀቁንም ተከትሎ ዩጋንዳ የ2022 የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሴካፋ የሴቶች ዋንጫ አሸናፊ ሆናለች፡፡
የውድድሩ አሸናፊ ሀገር ዩጋንዳ የወርቅ ሜዳሊያ እና የዋንጫ ተሸላሚ ስትሆን ፣ ተሸናፊዋ ብሩንዲ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ፣ ከሰዓታት በፊት ታንዛኒያን የረታችው ኢትዮጵያ በበኩሏ ሦስተኛ ሆና በመጨረሿ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች፡፡