ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ እስካሁን ተጫዋቾቹ ያልተመለሱለት ሰበታ ከተማ ቀጣይ ዕጣ ፈንታው ላይም አደጋ ተጋርጦበታል።
ሊጉ ከተቋረጠበት ሊጀመር የሁለት ቀናት ዕድሜ እየቀረው ሰበታዎች ልምምድ አለመጀመራቸው አስጊ ሆኗል፡፡ ከጅምሩ ጀምሮ እንከን ያላጣው ክለቡ ተጫዋቾቹ የጠየቁትን ጥያቄ መመለስ አለመቻሉን ተከትሎ እስከ አሁን ወደ ልምምድ አለመግባቻው የክለቡን ቀጣይነት አጠያቂ አድርጎታል፡፡
ሰበታ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከስምንት ዓመታት በኋላ 2012 ላይ በድጋሚ በማደግ የሦስተኛ ዓመት ተሳትፎውን እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ከተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ጀምሮ ከተጫዋቾች ወርሃዊ የደመወዝ ክፍያ አለመፈፀም ጋር ስሙ በተደጋጋሚ እየተነሳ የዘለቀው ክለቡ ዘንድሮም በተመሳሳይ ያለ መክፈል ጉዞው ከዓመቱ ጅማሮ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ እየተንከባለለ መጥቶ በክለቡ ላይ ከውጤት መጥፋት ባሻገር የባሰ ችግርን ለማድረስ ተቃርቧል፡፡ ዓመቱን በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጀምሮ በአጋማሹ ከተለያየ በኋላ በረዳት አሰልጣኙ ብርሀን ደበሌ በመመራት ላይ የሚገኘው ክለቡ ካደረጋቸው 25 የሊጉ ጨዋታዎች 23 የግብ ዕዳን ተሸክሞ በ20 ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ እየዳከረ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች እስኪቋረጡ ጊዜ ድረስ የመውረድ ስጋት ውስጥ እየባዘነ ቀሪ አምስት ጨዋታዎች ላይ በተዐምር ሊጉ ላይ ለመክረም ትልቅ ፈተና ከፊቱ የሚጠብቀው ቢሆንም በቀጣዩ ማክሰኞ ሰኔ 7 ዳግም ሊጉ ሲጀመር ክለቡን በተለየ መነሳሳት እንጠብቀዋለን ብለን ብናስብም አሁን ላይ ከብዙ ፈተናዎች ጋር በጭለማ ጉዞ ላይ ይገኛል፡፡
ቀጣዮቹን አምስት ጨዋታዎች ለማከናወን ክለቡ ለተጫዋቾቹ ግንቦት 23 በባህርዳር ሌክ ማርክ ሆቴል ተሰባሰቡልኝ ብሎ ጥሪ ቢያደርስም የክለቡ ተጫዋቾች “በተደጋጋሚ ስንጠይቅ የነበረው የደመወዝ ይከፈለን ጥያቄ እየተመለሰልን ባለመሆኑ ወደ ልምምድ አንደገባም”፡፡ በማለት ቁርጥ ያለ ሀሳባቸውን ቢገልፁም ክለቡ በምላሹ ማስታወቂያ በማውጣት “ተጫዋቾቹ በአፋጣኝ ወደ ልምምድ ተመለሱ” የሚል ማስጠንቀቂያ አውጥቷል። “የ2013 ከሁለት እስከ አራት የዘንድሮው ዓመት የአራት ወራት ደመወዝ ካልተፈፀመልን ለክለቡ ግልጋሎት አንሰጥም”፡፡ በማለት ለክለቡ ፅህፈት ቤት ፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፣ ለፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር ፣ ለኦሮምያ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ በተጨማሪነትም ለክልሉ እግር ኳስ ፌድሬሽን እና ለፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር 20ዎቹ የደመወዝ ጠያቂ ተጫዋቾች ተፈራርመው ደብዳቤ ማስገባታቸው የሚታወስ ሲሆን ፤ ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን “ጥያቄያችሁን እየተመለከትኩኝ ነው፡፡ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በቅርቡ ምላሽ ይሰጣችዋል”፡፡ የሚል ደብዳቤን በመልሱ ለተጫዋቾቹ ልኳል፡፡
ጥያቄያቸውን በደብዳቤ አቤት ብለው የነበሩት የክለቡ ተጫዋቾች ጉዳዩን ወደ ፊፋ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ እንዳሉ የገለፁልን ሲሆን የክለቡ የበላይ አካላት በበኩላቸው በጀት የለንም ከአቅማችን በላይ ነው በማለት ዝምታን መርጠዋል፡፡ ከዚህም መነሻነት የክለቡ ቀጣይ ህልውና የሚሸረሽሩ ጉዳዮች እየሸተቱ እየመጡ እንደሆነ ሰምተናል፡፡
ይህንንም አስመልክተን ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎችን ያነሳንላቸው የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ምንዳ ተከታዮቹን ምላሾች ሰጥተውናል።
“ክለቡ አደጋ ላይ ነው። እስከ ትናንት ድረስ በ6 ተጫዋቾች ነው ልምምድ እየተሰራ የነበረው። ከ6ቱ ተጫዋቾች ሦስቱ በዋና ሦስቱ በቢጫ ቴ ሴራ የተያዙ ናቸው። እርግጥ ትናንት ግብ ጠባቂው ሰለሞን ደምሴ ወደ ስፍራው ሄዷል። ዛሬ ደግሞ ጌቱ ኃይለማርያም እና ኃይለሚካኤል አደፍርስ ቡድኑን ይቀላቀሉታል። ሌሎቹም ተጫዋቾች ያለውን ነገር ተረድተው ወደ ልምምድ ይመለሳሉ ብለን እናስባለን።
“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ጥያቄ ጠይቆናል። ለተጫዋቾቻችን ደመወዝ እንዳልከፈልንም አምነናል። ግን እስከ ሰኔ አጋማሽ ድረስ በጀት አሰባስበን ደሞዙን እንደምንፈፅም ምላሽ ሰጥተናል። እኛ አሁን የምንጠብቀው ፌዴሬሽኑን ነው። ያለውን ነገር ተረድቶ ተጫዋቾቻችን ወደ ልምምድ እንዲመለሱ ያደርጋል ብለን እናስባለን።
“በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ክለቡ ይፈርሳል ብዬ አስባለው። ይህ እንዳይሆን ነው መረባረብ ያስፈልጋል የምንለው። ዓለም የሚያየውን ውድድር 5 ጨዋታ ፎርፌ ሰጥተን አናጠለሸውም። የሀገርም ገፅታ ይበላሻል። ስለዚህ እኛ እንደ አመራር አሁንም ጥረት ላይ ነን። ነገም የምንጠብቀው ነገር አለ። ግን በአፅንኦት የማስተላልፈው ነገር የክልሉ መንግስት፣ የከተማው አስተዳደር እና የከተማው ባለ ሀብቶች ተረባርበው ክለቡን ከገባበት አዘቅጥ እንዲያወጡት ነው። በዚሁ አያይዤ ተጫዋቾች ክለቡ ያለበትን ሁኔታ እንዲረዱ እንፈልጋለን። ክለቡ ተቸግሯል። እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ የአስተዳደር እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችም የሦስት ወር ደሞዝ አልተከፈለንም። ስለዚህ ተረድተውን ክለቡን ለማትረፍ እንዲጥሩልን እንማፀናለን ጥሪም እናስተላልፋለን።”