አሠልጣኝ ውበቱ አባተ መግለጫ ሰጥተዋል

👉” ግብፆች ወረዱ ያስባለው የእኛ መብለጥ ነው። በዛ ቀን ኢትዮጵያ ጥሩ ስለሆነች ግብፅ አንሳለች”

👉”ከጨዋታው በፊት ፎቶው ተዘቅዝቆ የተለጠፈ ተጫዋች በማግስቱ አሠልጣኙ ደፍሮ አምኖ ሲያሰልፍው ሜዳ ላይ መሞት ነው ያለበት”

👉”እንደተደሰትኩ በጣም የገባኝ ምንም የምሰራው ነገር ሳይኖረኝ በጣም አምሽቼ በመተኛቴ ነው”

👉” . . . የፈለገ ተዐምር የምትሰራ ሰው ብትሆን ያለ ተጫዋቾቹ ምንም ነህ”

👉” ምክንያታዊ የሆነ ትችት የሚሰጡ አሉ። አለፍ የሚለውን ነገር መሸከም ነው ያልቻልነው ”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣዩ ዓመት በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት በሚከናወነው የአህጉሪቱ ውድድድ ላይ ለመሳተፍ በምድብ 4 ከማላዊ፣ ግብፅ እና ጊኒ ጋር ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል። ወደ ማላዊ ሊሎንግዌ አምርቶ የምድብ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎችን ከማላዊ እና ግብፅ አቻው ጋር ያደረገው ቡድኑ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰ በኋላ ዛሬ መግለጫ ተሰጥቷል። ከ9 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ቴክኒካዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳቱዮች በቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና የጽህፈት ቤት ሀላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ማብራሪያ ሰጥተዋል። በቅድሚያም አሠልጣኙ ያጋሩትን ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርበናል።

“የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ሁለት ጨዋታዎችን ለማድረግ ወደ ማላዊ ተጉዘናል። ጉዞዋችንም ጥሩ ነበር። በጤና በኩል በመጀመሪያው ጨዋታ ከተፈጠረ አንድ ችግር ውጪ ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ ሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ነበሩ። የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ በተለይ ከእረፍት በፊት በነበሩ ቅፅበቶች ማላዊዎች ሁለት ተከታታይ የፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ችለዋል። እነዛንም ወደ ጎልነት ተቀይረው ነበር። ከእረፍት መልስ ምንም እንኳን ማሸነፍ ባንችልም መጠነኛ ለውጦችን አድርገን አንድ ጎል አስቆጥረን 2ለ1 ተሸንፈናል። ጨዋታው ሁለት አይነት መልክ ነበረው። በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም እንኳን ከሜዳችን ወተን ለመጫወት ጥረት ብናደርግን ወደእኛ የሚመጡ የመልሶ ማጥቃት እና ቀጥተኛ አጨዋወቶችን ለመቆጣጠር ተቸግረን ነበር። ነገርግን በአጠቃላይ እንደ አንድ ከሜዳችን ውጪ እንዳደረግነው ጨዋታ ለእኛ እና ከተጫዋቾቹ ጥሩ ሞራል የሰጠ ጨዋታ ነበር። ጥሩ ተጫውተናል። በዛ ጨዋታ የቡድናችንን ክፍተት ከማየት በተጨማሪ ትንሽ ብናሻሽል ውጤቱን ይዘን መውጣት እንደምንችል ነበር የተመለከትነው። ከተጋጣሚ አሠልጣኝ እና ደጋፊዎች የነበረው ግብረ መልስም በጣም ጥሩ ነበር።

“ሁለተኛው ጨዋታ የግብፅ ጨዋታ ነው። ይህ ጨዋታ ጠንካራ ጨዋታ እንደሚሆን አስቀድመን ጠብቀን ነበር። በእርግጥም ጨዋታው ጠንካራ ነው። የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ሁለት ጎሎችን አስቆጥረናል። በተጨማሪም ከማላዊው ጨዋታ በተለየ አቀራረብ የሚመጣ ቡድን ስለሆነ እድሎችን በተደጋጋሚ ለመፍጠር በር እንደከፈተልን አይተናል። ሁሉም ተጫዋቾች በጥሩ አቋም እና ተነሳሽነት ጨዋታውን ለመጨረስ እስከ መጨረሻው ተጫውተዋል። ከእረፍት መልስ ቀድመን ያስቆጠርነውን ጎል አስጠብቀን ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ለመውጣት ያደረግነውም ነገር የተሳካ ነው የነበረው። በእነርሱ በኩል እንደ ወትሮው በጠበቅነው ደረጃ አደጋ የሚፈጥር ነገር ጨዋታው ላይ አልተከሰተም ብሎ መናገር ይቻላል። በአጠቃላይ በሁለቱም ጨዋታ ላይ ጥሩ ነገር ነበረን ማለት እችላለው። ግብፅን ማሸነፍ ትልቅ ነገር እንደሆነ ይሰማኛል። ግን ከዛ በላይ በወጥነት ከሜዳ ውጪ ያደረግናቸውን ትላልቅ ጨዋታዎች በተረጋጋ መንገድ ለማከናወን መሞከራችን ቡድናችንን የበለጠ ተስፋ እንድንጥልበት አድርጎናል።” በማለት ንግግራቸውን ካሰሙ በኋላ ከብዙሃን መገናኛዎች በቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይዘዋል።

ስለ ግብፁ ጨዋታ ዝግጅት…?

“ከሁሉም ጨዋታዎች በፊት የራሳችንን ከተመለከተው ዝግጅት በተጨማሪ ተጋጣሚያችንን የምናይበት ዝግጅት አለን። ለግብፅም እንደዚሁ አድርገናል። ምን አይነት ጨዋታ ነው የሚጫወቱት እንዲሁም እንዴት ብንጫወት ነው የምንበልጣቸው የሚለውን ጨዋታቸውን በማየት ተዘጋጅተናል። ልምምድ ላይም ይሄንን ተንተርሰን ሰርተናል። እነርሱ ለእኛ ያነሰ ግምት ነው የሚሰጡት። ግን እኛ እነሱን እንደምናይ እነሱም እኛን ያዩናል። መጨረሻ ላይ ግን አሰላለፋቸውን ስናይ በሦስት አጥቂ እና ሦስት ተከላካይ ለመጫወት ነበር ሀሳባቸው። ይህ ከኋላ ምንም አይነት ችግር አይኖርም የሚል ሀሳብ እንዳላቸው ጠቁሞናል። ኳሱን መስርቶ ከመውጣት በተጨማሪ በእነርሱ የመከላከል ወረዳ ሦስት አጥቂ ከሦስት ተከላካይ ጋር ነው የሚገናኘው ፤ ስለዚህ ከሦስቱ ተከላካዮች ጀርባ የሚገኘውን ቦታ መጠቀም አንዱ ሀሳባችን ነበር። ሁለተኛው ነገር ደግሞ በማላዊው ጨዋታ የቡድናችን የመጠቂያ ኳሶች የሚነሱት ከቀጥተኛ አጨዋወት ነበር። እነዛን ቀጥተኛ ኳሶች ከምንጫቸው ማቆም ካልቻልን በእኛ የመከላከል ክፍተት ለእነርሱ ብዙ እድል እንሰጣለን። ስለዚህ እነርሱ ከሚያስቡት በተቃራኒ መግባት አዋጪ ነው ብለን በማሰብ ከራሳቸው እንዳይጀምሩ እና ፕሬስ ማድረግን መርጠናል። ሌላው የተለየው ነገር ተጫዋቾቹ እኛ ከምናነሳሳቸው በላይ እነርሱ ራሳቸው የሆነ ነገር ለማግኘት ተነሳስተው ነበር። ይሄም ሜዳ ላይ ከኳስ ውጪ የነበረውን ነገር ከፍ እንዲል አድርጎታል። ይሄ ነገር ዝም ብሎ የመጣ ነገር አይደለም። በእንቅስቃሴ ደግሞ የምናያቸው ነገሮች በቀጣይም እንድንደፍራቸው አድርጎናል።”

ከሜዳ ውጪ ስለመጫወት…?

“ተፅእኖ አለው። ተጫዋቾቹን ገና ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ስናገኛቸው ይሄንን ነገር ነግረናቸዋል። እንደ ሰበብ እንዳንወስደው ተማምነናል። በዚህ ውስጥም ቢሆን ያለንን አሟጠን መጠቀም እንዳለብን ተነጋግረን ተዘጋጅተናል። ማላዊ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ከመጀመሪያው ጨዋታ በኋላ በነበረ የእራት ግብዧ በጨዋታው ባሳየነው እንቅስቃሴ እንደተደሰቱ እና ማላዊያንም በጣም እንደተደመሙ ነግረውን ቀና እንድንል አድርጋችሁናል ብለውናል። ይሄ ትልቅ የስነ-ልቦና መነሳሳት ይፈጥራል። ተጫዋቾቹን ማነሳሳተ እና የሚችሉትን እንዲያወጡ ለማድረግ ተሞክሯል። ከጨዋታው በፊት ፎቶው ተዘቅዝቆ የተለጠፈ ተጫዋች በማግስቱ አሠልጣኙ ደፍሮ አምኖ ሲያሰልፍው ሜዳ ላይ መሞት ነው ያለበት። የሆነው ሆኖ ከጨዋታው የሁላችንም ቤተሰቦች የሚጠብቁት ነገር ነበር እና ይሄ መነሳሳት ፈጥሯል።”

ግብፅን ስለመግጠም…

“ኢትዮጵያ ቡና ሆኞ የግብፅን ቡድን ገጥሜያለው። ይሄ ሁለተኛ ግጥሚያዬ ነበር። ለተጫዋቾቹ ተመሳሳይ ነገር ነበር ስነግራቸው የነበረው። የዛኔ ትልቅ ቡድን ነበር የገጠምነው። ነገር ግን የተጫወትንበት መንገድ ትዝ ይለኛል። ጥሩ ነበር። ይህንን አጨዋወት እንድንደግም ፍላጎት ነበረኝ። እርግጥ ትልቅ ቡድን ነበር የምንገጥመው። የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚ እና የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የወደቀን እና ጥሩ ታሪክ ያለውን ቡድን ነበር የምንገጥመው። ይህ ቢሆንም የሆነ ነገር ማድረግ እንደምንችል ይሰማኝ ነበር። ቅድመ ጨዋታ ላይም ተጫዋቾቹን ከማነሳሳት ውጪ የተለየ ነገር አላደረግንም። ጨዋታው እየተከናወነ ግን የሚሰማህ ስሜት አለ። ተጫዋቾቹ ያደረጉት ነገር ደግሞ የበለጠ የራስ መተማመናችን ከፍ እንዲል አድርጎታል። ግን መጠንቀቅ እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር። ምክንያቱም ግብፅ ግብፅ ነች። ጨዋታውን በየሆነ መንገድ ልትነጥቅህ ትችላለች።”

ከውጤቱ በኋላ ምን ተሰማህ…?

“በጣም ደስ ብሎኛል። ይሄንን መሸሸግ አልፈልግም። እንዳልነው ትልቅ ቡድን ነው ያሸነፍነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ጊዜ ብዙ ጎሎችን ነበር የሚያስቆጥሩብን። ይህ የሚፈጥረው ቁጭት አለ። ስለዚህ በእንደዚህ አይነት ጨዋታ እነርሱን ማሸነፍ ደስ ይላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከሜዳችን ውጪ መሆኑ ደግሞ አስደስቶኛል። እንደተደሰትኩ በጣም የገባኝ ምንም የምሰራው ነገር ሳይኖረኝ በጣም አምሽቼ በመተኛቴ ነው። በተጨማሪም በዚህ ማሸነፍ ውስጥ ለሌሎች ምን ያህል ደስታ እንደሰጠን ማሰብም ትልቅ ነገር ነው። ግን ጨዋታ ስለሆነ ስለ ቀጣዩም ነገር ማሰብ ስላለብን በነጋታው ወደዛ ነው ያመራነው።”

ከሁለቱ ጨዋታዎች የተቆጨህበት ነገር…?

“ከግብፁ ጨዋታ የተቆጨሁበት ነገር የለም። ከበቂ በላይ ነው። በማላዊው ጨዋታ ግን የተቆጠሩብን ጎሎች ላይ የፈጠርናቸው ስህተቶች ናቸው። ይሄ ባይሆን ውጤቱ ሊቀየር ይችል ነበር። በተጨማሪም የተንቀሳቀስንበት መንገድ ቢያንስ አንድ ነጥብ እንኳን እንድናገኝ መሆን ነበረበት። ግን አልሆነም። ተጫዋቾቹ የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።”

በግብፁ ጨዋታ ስለነበረው ነገር…?

“በጨዋታው ሁሉም ነገር ነበር። ኳስ ቁጥጥር፣ የግብ እድል መፍጠር እና የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። ከእረፍት በኋላ ጨዋታውን ከመቆጣጠር አንፃር በሚገኙ አጫጭር እና ፈጣን እንቅስቃሴዎች ለማስቆጠር ነው ያሰብነው። ግን እነርሱ ያን ያህል ብልጫ ወስደው የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አልተመለከትኩም። ኳሱን የምንቆጣጠረው ጨዋታውን ለመቆጣጠር ነው። ይሄንን ለማድረግ ግን ገና ነን። 90 ደቂቃ እንደዛ እየተጫወትን መቆየት ገና ነው። የሆነ ቀን ግን እንደሚመጣ አስባለው።”

ስለ ጋቶች ብቃት…?

“ጋቶች አንዱ ተጫዋቻችን ነው። በጣም ጥሩም ተንቀሳቅሷል። ተቀይሮ በገባበት በመጀመሪያው ጨዋታም ሆነ በሁለተኛው ጨዋታ በመከላከሉም ሆነ ጨዋታውን በማቅለል ትልቅ ሚና ነበረው። በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የመጫወት ዕድሉም ማስቀጠሉ አይቀርም።

ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው ቆይታ ላይ ስለነበረው የተጫዋቾች ምርጫ…?

“ሁለት ዓመት ሊሞላ ነው። ከጅምሩ ጀምሮ ይዘናቸው የመጣናቸው ተጫዋቾች አሉ። ያስቀመጥነው ነገር አለ። በዛ ባስቀመጥነው መስመር ውስጥ በሁሉም ነገር እየተጣሩ እያለፉ የመጡ ተጫዋቾች አሉ። በዚህ ውስጥ ከእኛ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተጫዋቾች ሁሉ ድጋፍ በመስጠት በስህተታቸውም (እግር ኳሳዊ) ድጋፍ እየሰጠን እዚህ ደርሰናል። ከአንድ አሠልጣም ይህ ይጠበቃል። የፈለገ ተዐምር የምትሰራ ሰው ብትሆን ያለ ተጫዋቾቹ ምንም ነህ። የቀጣናቸውን አስተምረን የምንመልስበት ጊዜ ነበር። እግር ኳሳዊ ስህተቶችን የሚሰሩትንም ድጋሚ እድል እየሰጠን ለበርካታ ጊዜ የታገስነሰቸው እና የተቀየሩ እንዲሁም ሳይቀየሩ አብረውን የሌሉ አሉ። ስለዚህ በእኛ ደረጃ ምንችለውን እያደረግን ነው። አሁን ቡድኑ ወደ ሆነ መስመር እየመጣ እንደሆነ ይሰማኛል። በሀሳብም በአጨዋወትም ቡድኑ ከሚፈልገው ነገር ጋር አብዛኞቹ እየተዋሀዱ መጥተዋል።”

ቡድኑ ላይ ስለሚሰነዘር ትችት…?

“ቦታው ለዚህ ነገር ቅርብ እና ክፍት ነው። ከትችቶቹ የሚጠቅምህን እየወሰድክ የማይሆኑትን ባላየ እያለፍክ መሄድ ነው። ግላዊ እና ከቤተሰብ ጋር የተገናኙ ነገሮች ሲሆኑ እንደ ሰወኛ በስጨት የምትልበት አጋጣሚ ይፈጠራል እንጂ የትልቅ ሀገር ብሔራዊ ቡድንን እያሰለጠንክ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ማለት አይደለም። ተፅዕኖ የለውም ማለት ግን አይቻልም። ተጫዋቾች ጋር ይጋባል። እኔ ግራ የሚገባኝ ነገር አለ። እኛ ባለሙያዎች፣ የውጪ ሰዎች የሚሰጡይ እና እዚህ የሚሰጠው ነገር ያምታታኛል። ይህ እኔም ተጫዋቾቹም ሆነ ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ከእንደሱ አይነት ጫና የምንጠበቅበት ነገር ቢኖር ጥሩ ነው። ምክንያታዊ የሆነ ትችት የሚሰጡ ሰዎች እና ባለሙያዎች አሉ። አለፍ የሚለውን ነገር መሸከም ነው ያልቻልነው። እኔ ልኖርም ሆነ ላልኖር እችላለው። የሚኖረውን ሰው ግን በደንብ መደገፍ አለብን።”

ስለ ግብፅ ብቃት…?

“ወደ ኋላ ልመልስህ እና ኒጀርን ስንገጥም ደካማዋን ኒጀር ተባለ። ከዛ ማዳጋስካርን ገጠመን የዛኔም እንደዛው። እኛ ያሸነፍናቸው ቡድኖች ሁሉ ሲሸነፉ ደካማ ከሆኑ እንዴት እናድርግ። ግብፅ አሠልጣኝ ቀይራለች። የተወሰኑ ተጫዋቾችንም አታለች። ይሄ የተወሰነ ተፅዕኖ ይኖረዋል። እንደ ብሔራዊ ቡድን ግን እኛ በልጠናል። ስለዚህ ክሬዲቱን ለተጫዋቾቹ እንስጥ። ግብፆች ወረዱ ያስባለው የእኛ መብለጥ ነው። በዛ ቀን ኢትዮጵያ ጥሩ ስለሆነች ግብፅ አንሳለች። በዛ ጨዋታ የሚችሉትን ሞክረዋል። ተጫዋችም ቀይረው ሞክረዋል። ግን የእኛ ተጫዋቾች በልጠው ነበር። ግብፅ ደክማ አይመስለኝም። ምክንያቱም ከሦስት ቀን በፊት ግብፅ ጊኒን አሸንፋለች። ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ ቡድን ከግብፅ ተሽሎ ስለነበረ ነው ያሸነፈው። በተሸነፍንበትም ሆነ ባሸነፍንበትም ጨዋታ ተጋጣሚ ደክሞ ከሆነ ያስቸግራል። ደግነቱ ጨዋታው በቲቪ ስለታየ ቡድኑ የነበረውን ብቃት ሁሉም ሰው አይቶታል። በጨዋታው ጥሩ ልንጫወት እንደምንችል ላስብ እችላለው ግን አምስት ስድስት የግብ እድል እንፈጥራለን ብዬ አላስብም ነበር።”

ስለ ኮንትራት…?

“ስለ ኮንትራት የተጀመረ ንግግር የለም። በቀጣይ ጊዜያት የምናወራበት ይሆናል።”