የፌዴሬሽኑ ምርጫ የሚደርግበት ወቅት ታውቋል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚመራውን ፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ለማከናወን የሚደረግበት ወቅት ይፋ ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አቶ ኢሳያስ ጅራ እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የመሪነት ጊዜያቸው በመገባደዱ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን የሚመራው ፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን ለመምረጥ በነሀሴ ወር ምርጫ እንዲደረግ ተወስኗል ሲል ፌድሬሽኑ ገልጿል፡፡ ዛሬ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚዎች ባካሄዱት አስቸኳይ ስብሰባም ነሐሴ 21 እና 22 በጎንደር ከተማ እንዲደረግ ወስነዋል፡፡

ነሐሴ 21 በጎንደር ከተማ የ2014 የበጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም እና የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የሚካሄድበት ቀን ሲሆን ነሐሴ 22 ደግሞ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን የሚመሩ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ የሚከናወን ይሆናል።ባሳለፍነው ግንቦት 7 ቀን 2014 በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ አዲስ የመተዳደርያ ደንብ መፅደቁ እንዲሁም የአስመራጭ እና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች መሠየማቸው የሚታወስ ነው።

ይህ መተዳደሪያ ደንብ በጉባኤ ቀርቦ በአባላቱ በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ መጸደቅ ያለበት በመሆኑ የተወሰነ ጊዜ የወሰደ እና የምርጫ ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ለአባላት የሚቀርቡ ሰነዶች በመተዳደሪያ ደንቡ የተቀመጠውን ጊዜ ጠብቀው መድረስ ያለባቸው ስለሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የምርጫው ጠቅላላ ጉባዔ ነሐሴ 21 እና 22/2014ዓ.ም እንዲካሄድ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዛሬው እለት በመወሰን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ከአሁኑ እንዲጀመሩ ለጽ/ቤቱ አቅጣጫ ተሰጥቷል ሲል ፌዴሬሽኑ በድረገጹ አብራርቷል።