የአሠልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 1-2 አርባምንጭ ከተማ

አርባምንጭ ከተማ ሲዳማ ቡናን ከረታበት ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች አስተያየት ተረክቧል።

መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ


ከሊጉ እረፍት በኋላ ስላደረጉት እንቅስቃሴ…?

“ካለፉት ጨዋታዎች አንዳንድ ነገሮችን እየገመገምክ ትመጣለህ። በጨዋታው ብልጫ ወስደን ነው የወጣነው። ቅድሚያ ወስደን ከወጣን በኋላ ነገሮችን በጥንቃቄ ነው ለመከወን የሞከርነው። በቁጥሮች ደረጃ መጠነኛ ልዩነቶች ቢኖሩም የእረፍት ጊዜያችንን በሚገባ ተጠቅመናል።”

ለወጥ ስላለው የቡድኑ እጨዋወት…?

“ከሌላው ጊዜ ያደገ የኳስ ቁጥጥሮች ይኖራሉ ፤ ጠብቁ። አንዱ መከላከል ኳስን ለባለ ጋራ አለመስጠት ነው። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች በቀጣይ ጊዜያት እናሳድጋለን።”

ስለኤሪክ ካፓይቶ ብቃት…?

“ከጨዋታው በፊት ተነጋግረናል። በኬንያ ሊግ በሦስት ዓመት 2 ጊዜ ኮከብ ግብ አግቢ የሆነ ተጫዋች ነው። ግን አሁን በዛ ደረጃ አልነበረም። ስለዚህ በቀሩት 5 ጨዋታዎች ከአንተ የምንጠብቀው ነገር አለ ብለነው ነበር። እርሱም በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ጥሩ እሰራለው ብሎ ቃል ገብቶ ነበር። የገባውንም ቃል ሜዳ ላይ አደረገው።”

በደረጃ ሰንጠረዡ እድገት ስለማሳየታቸው…?

“ዘንድሮ የመጀመሪያ ዓመታችን ነው። አሁን ወደ ሰባተኛ ደረጃ ተጠግተናል። ይህ ቀላል አይደለም። ቀሪዎቹን ጨዋታዎች ደግሞ ፈጣሪ ፈቅዶ በድል የምንወጣ ከሆነ ከዚህ የተሻለ ደረጃ ላይ መጨረስ እንችላለን። ለመጀመሪያ ዓመት ግን ይሄ ቀላል አይደለም። መልካም ነው።”

ወንድማገኝ ተሾመ – ሲዳማ ቡና


ጨዋታው እንዴት ነበር…?

“ሁለቱም አጋማሾች ለእኔ በስህተቶች የተሞሉ ነበሩ። መጀመሪያም በተከላካይ ስፍራ የጊት አለመኖር ዋጋ እንደሚያስከፍለን እምነት ነበረኝ። ይህ ቢሆንም በመጀመሪያው አጋማሽ እና በሁለተኛው አጋማሽ የተቆጠሩብን ጎሎች (ሁለቱ ጎሎች በመጀመሪያው አጋማሽ መቆጠራቸው ልብ ይሏል) የተከላካዮቻችን አለመግባባት የታየበት ነበር። እንደዚህም ሆኖ በመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ የምናገኛቸውን ኳሶች ስተናል። አጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ነበር። ግን ከጠበኩት በታች ነው።”

ሀብታሙ ስለተሰጠው ሚና…?

“በጨዋታው ተጫዋች ቀይ ወጣብን። ሲወጣብን በ3-5-2 ለመጫወት አሰብን (በጎዶሎ ተጫዋች ይህ አሰላለፍ አይኖርም)። ስለዚህ ይገዙ እና ሳላዲንን ከፊት አደረግንና እርሱ ከመስመርም ወደ መሐልም እየገባ እንዲጫወት ድጋጅ ሰጠነው።”

ያኩቡ በቀይ ከወጣ በኋላ ጨዋታውን ስለከወኑበት መንገድ…?

“ከቀይ ካርዱ በኋላ ሀሳቤ 100 በ100 ተሳክቶልኛል። ምክንያቱም በጎዶሎ ተጫዋቾች ተጭነናቸው እየተጫወትን ነበር። ብዙ የጎል ማግባት አጋጣሚዎችን አግኝተን አልተጠቀምንም። ስለዚህ ያኩቡ መውጣቱ እንደ ቡድን ቢጎዳኝም ቀይረን ያስገባናቸው ተጫዋቾች የተሻሉ ነበሩ። በዚህም ደስተኛ ነኝ።”