ከአህጉራዊ ማጣሪያዎች በኋላ ዳግም በተመለሰው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ የጨዋታ ሳምንት የመክፈቻ መርሐግብር አርባምንጭ ከተማዎች ሲዳማ ቡናን በመርታት ደረጃቸውን አሻሽለዋል።
አርባምንጭ ከተማዎች የተሻለ አጀማመርን ባደረጉበት ጨዋታ አውንታዊ ሆነው በመጀመር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲታትሩ አስተውለናል። በሙከራዎች ረገድ እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያ ሙከራ የተመለከትነው በ17ኛው ደቂቃ ነበር። ሲዳማ ቡናዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት የፈጠሩትን ግልፅ አጋጣሚ ይገዙ ቦጋለ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።
በሂደት በጨዋታው ተፅዕኗቸው እየጨመረ የመጡት ሲዳማ ቡናዎች ኳስን በትዕግሥት በመቀባበል ከኳስ ውጪ ጠቅጠቅ ብለው ለመከላከል ይሞክሩ ከነበሩት አርባምንጭ ተጫዋቾች በስተጀርባ ኳሶችን ማድረስ ጀምረዋል። 27ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከተከላካዮች ጀርባ ያደረሰውን ግሩም ኳስ ተጠቅሞ ይገዙ ቦጋለ በቀኝ እግሩ ያደረገው ሙከራ በይሳቅ ተገኝ የከሸፈበት እንዲሁም በ30ኛው ደቂቃ ያኩቡ መሀመድ ከማዕዘን ከተሻማ ኳስ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን አድርገዋል።
ሲዳማ ቡናዎች ግብ ሊያስቆጥሩ በመሰለበት ወቅት በ33ኛው ደቂቃ አርባምንጭ ከተማዎች ሳይጠበቁ መሪ መሆን ችለዋል። በሜዳው የላይኛው ክፍል ከተነጠቀ ኳስ እንዳልካቸው መስፍን በግሩም ሁኔታ አንጠልጥሎ ያቀበለውን ኤሪክ ካፖዬቶ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል።
በአንድ ደቂቃ ልዩነት አርባምንጮች መሪነታቸውን ሊያሳድጉ የሚችሉበትን አጋጣሚ አህመድ ሁሴን ከተከላካይ ጀርባ በተጣለለት ኳስ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከግቧ በኋላ ተረጋግተው ወደ ጨዋታ ለመመለስ የሞከሩት ሲዳማዎች በ37ኛው ደቂቃ አቻ ሆነዋል። ሲዳማዎች ከቆመ ኳስ በፍጥነት ሳላዲን ሰዒድ ያስጀመረውን ኳስ ራሱ ሳጥን ውስጥ በመገኘት ቡድኑን ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ አስቆጥሯል።
ተነቃቅቶ በቀጠለው ጨዋታ በ40ኛው ደቂቃ ሲዳማ ቡናዎች በፈጣን ማጥቃት ሂደት በፈጠሩት አጋጣሚ ሰልሀዲን ሰዒድ እና ዳዊት ተፈራ አከታትለው ያደረጓቸው ሙከራዎች ሳይሰምርላቸው ቀርቷል።
አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሦስት ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩ ያኩቡ መሀመድ በራሱ ሳጥን ውስጥ ኳስ በሚቀበልበት ወቅት በአግባቡ አካባቢውን መቃኘት ባለመቻሉ በአቅራቢያው የነበረው ኤሪክ ካፓይቶ ኳሱን በሚነጥቅበት ወቅት በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ካፓይቶ ዳግም አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ በማድረግ አጋማሹን ፈፅመዋል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር በነበረው ሁለተኛ አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በተሻለ ኳስ በማንሸራሸር የአቻነት ግብ ሲፈልጉ በአንፃሩ አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ በጥንቃቄ ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል።
ነገር ግን በ56ኛው ደቂቃ አርባምንጭ ከተማዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሂደት ወደ ፊት ለመድረስ ያደረጉትን ጥረት ባልተገባ መልኩ ለማቋረጥ ጥረት ያደረገው ያኩቡ መሀመድ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ መወገዱን ተከትሎ የጨዋታ መንፈስ በተወሰነ መልኩ ተለውጧል።
በሙከራ ረገድ ምንም እንኳን ሲዳማ ቡናዎች የተሻሉ ሆነው ቢዘልቁም አርባምንጭ ከተማዎች ከቀይ ካርዱ በኋላ ከመጀመሪያው ደቂቃዎች በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት አስተውለንባቸዋል።
በ54ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከሳጥን ውጪ ያደረገው እንዲሁም ሳላዲን ሰዒድ በሁለት አጋጣሚዎች ማለትም በ64ኛው ደቂቃ በረጅም ከተከላካይ ጀርባ ከተጣለለት ኳስ ያደረገው ሙከራ እንዲሁም በ67ኛው ደቂቃ ወደ ግራ ካደላ አቋቋም ከተገኘ የቅጣት ምት ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ያደረገው እና ይስሀቅ ያዳነበት ኳስ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች ነበሩ።
በቀሪዎቹ ደቂቃዎች አርባምንጮች በተወሰኑ አጋጣሚዎች በተሻጋሪ ኳሶች እና በመልሶ ማጥቃቶች በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ኤሪክ ካፓይቶን ታሳቢ በማድረግ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ምንም እንኳን በቁጥር ቢያንሱም ከጨዋታው ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ጥረት ቢያደርጉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የነበረባቸው ውስንነት ፍላጎታቸውን እውን እንዳያደርጉ አግዷቸዋል።
ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማዎች አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ አርባምንጮች ነጥባቸውን ወደ 34 በማሳደግ ደረጃቸውን ወደ 7 ከፍ ሲያደርጉ በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ በነበሩበት 40 ነጥብ በመርጋት በሁለተኛ ደረጃ የማጠናቀቅ ውጥናቸው ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።