ጥሩ ፉክክር በተስተዋለበት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ፈረሰኞቹ ከጣናው ሞገዶቹ ጋር አቻ ተለያይተዋል።
ተጠባቂው ጨዋታ ገና ከጅምሩ ለዐይን ሳቢ ሆኖ ተገኝቷል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎችም ቡድኖቹ የሚገኙ ኳሶችን በቶሎ ወደ ግብነት ለመቀየር ሲጥሩ ተስተውሏል። በቅድሚያ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ኖሯቸው መንቀሳቀስ የያዙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ3ኛው ደቂቃ አለልኝ አዘነ ጋቶች ፓኖም ላይ የሰራውኝ ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ፍሪምፖንግ ሜንሱ ሞክሮት ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በመቀመጫ ከተማቸው የሚጫወቱት ባህር ዳሮች በተመስገን ደረሰ አማካኝነት ጥሩ ጥቃት ሰንዝረዋል። ገና ከጅምሩ ሙከራዎች የበረከቱበት ጨዋታው በ10ኛው ደቂቃም ሌላ የሰላ ጥቃት ተስተናግዶበታል። በዚህም በደቂቃዎች ልዩነት ከርቀት ቻርለስ ሉክዋጎ ላይ ግብ ለማስቆጠር የሞከረው ኦሴ ማውሊ በሁለተኛው ሙከራ ለግብነት ቀርቦ ነበር።
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እያስመለከተ የቀጠለው ጨዋታ ቀጣዩን ሙከራ በ29ኛው ደቂቃ አስተናግዶ መሪ አግኝቷል። በዚህም አለልኝ ጫና ፈጥሮ የነጠቀውን ኳስ ለማውሊ አመቻችቶለት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ሲያደርግ የነበረው አጥቂ ከሳጥኑ ጫፍ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎት የጣናው ሞገዶቹን ቀዳሚ አድርጓል። ይሁ አጥቂ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር በሳጥኑ የቀኝ ቦታ ተገኝቶ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።
ወደ ጨዋታው ለመመለስ መጣር የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ብዙም ሳይቆዩ ሀሳባቸው ፍሬ አፍርቷል። በዚህም ዓሊ ሱሌይማን ቸርነት ጉግሳ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል የዕለቱ አልቢትር ማኑኤ ወልደፃዲቅ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተው አምበሉ ሀይደር ሸረፋ ወደ ግብነት ቀይሮታል። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳይስተናገድ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡት ባህር ዳሮች በተደጋጋሚ የጊዮርጊስን የመከላከል ወረዳ ሲጎበኙ ነበር። በተለይ በ50ኛው ደቂቃ ማውሊ እንደለመደው ከሳጥን ውጪ አክርሮ የሞከረባቸው እንዲሁም ከደቂቃ በኋላ አለልኝ ከሳጥኑ ጫፍ ወደ ግብ የላከባቸው ኳሶች ለመቆጠር የተቃረቡ ነበሩ። በተቃራኒው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫና የበዛባቸው ፈረሰኞቹ ቀስ በቀስ እድገት እያሳዩ መጥተዋል። በቅድሚያም በ54ኛው ደቂቃ በአማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት ጥቃት አድርሰው ተመልሰዋል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም በ58ኛው ደቂቃ ሔኖክ አዱኛ ካልተጠበቀ ቦታ የግቡን መረብ ለማግኘት ጥሯል።
ሁለት የአማካይ መስመር ተጫዋቾችን በመቀየር ይበልጥ ለመጠናከር ያሰቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ61ኛው ደቂቃ የተጫዋች ለውጣቸው ዋጋ አስገኝቶላቸው መሪ ሆነዋል። በዚህም ጋቶች ፓኖምን ቀይሮ የገባው ከነዓን ማርክነህ የሜዳውን ሳር ከረገጠ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ሱሌይማን ሀሚድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በሩቁ ቋሚ ቆሞ በመጠበቅ እርጋታ በተሞላበት ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሮታል።
ከመምራት ወደ መመራት የተሸጋገሩት ባህር ዳሮች ዳግም ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር ይዘዋል። የቡድኑ አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱም የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በማስገባት አንዳች ነገር ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። በዚህም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሩብ ሰዓት ሲቀረውም አምበሉ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ከርቀት መሬት ለመሬት ከሞከረው ከደቂቃ በኋላ የጊዮርጊስ የአቻነት ግብ የተገኘበት የፍፁም ቅጣት ምት በተሰጠበት ተመሳሳይ ቦታ ላይ አቤል ያለው ግርማ ዲሳሳ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል የፍፁም ቅጣት ተሰጥቷል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ማውሊ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጎታል። ግቡን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮ የውድድር ዓመት በአንድ ጨዋታ ከአንድ ጎል በላይ ጎል ሲቆጠርበት ለመጀመርያ ጊዜ ሆኖ ተመዝግቧል። ለመጨረሻ ጊዜ ፈረሰኞቹ ከአንድ በላይ ጎል ያስተናገዱት በ2013 የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማን 3-2 ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ ነበር።
በቀሪ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ በተሻለ አጥቅቶ አሸናፊ ለመሆን ቢጥርም በእጃቸው የገባውን አንድ ነጥብ አሳልፎ ላለመስጠት የጣሩትን የባህር ዳር የኋላ መስመር ተጫዋቾች አስከፍቶ መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ፍፃሜውም አግኝቷል።
ውጤቱን ተከትሎ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 55 ሲያደርስ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ በ30 ነጥቦች በ12ኛ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።