የሰበታ ከተማ ተጫዋቾች ወደ ልምምድ እንዲመለሱ ፌዴሬሽኑ አዟል

ከደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጋር በተገናኘ ልምምድ ያልጀመሩት የሰበታ ተጫዋቾች ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ወስኗል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ሰበታ ከተማ 21 ተጫዋቾቹ ከደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ ልምምድ ሳይጀምሩ እንደቀሩ ዘግበን እንደነበር ይታወቃል። ተጫዋቾቹ ‘በውላችን መሰረት ክፍያው ይፈፀምልን ካልሆነ ወደ ልምምድም ሆነ ውድድር አንሄድም ፤ ፍትህ ይሰጠን’ በማለት ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ አስገብተው የነበረ ሲሆን የፌዴሬሽኑ የፍትህ አካልም ጉዳያቸውን ሲመረምር ቆይቶ በዛሬው ዕለት ውሳኔ ማስተላለፉን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የዲሲፕሊን ኮሚቴ ዛሬ ባወጣው ውሳኔ ላይ የተጫዋቾቹን ጥያቄ በመንተራስ ክለቡ ምላሽ እንዲሰጥ ተደርጎ ምላሽ መስጠቱ ተጠቁሟል። በዋናነት የተነሳው የደሞዝ ጉዳይ ላይ ክለቡ “ለተጫዋቾች፣ ለአስተዳደር እና ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች የመጋቢት እና የሚያዚያ ወር ደሞዝ ባጋጠመው የበጀት ችግር ምክንያት ያልተከፈለ ሲሆን የግንቦት እና የሰኔ ወር ደሞዝን ጨምሮ ለመክፈል የክለቡ ቦርዱ የተለያዩ የገቢ ምንጭ እያፈላለገ ነው” በማለት እስከ ሰኔ 20 ድረስ ክፍያ የምንፈጽም ይሆናል ብለው የሰጡትን ምላሽ በመጥቀስ አመልካቾች በውላቸው መሰረት አገልግሎት እየሰጡ ደመወዝ መጠየቅ ይገባቸዋል ነገር ግን አገልግሎት ሳይሰጡ ወይም በጨዋታ ሳይካፈሉ አገልግሎት ላልሰጡበት ጊዜ ደሞዝ የሚጠይቁበት ሁኔታ የለም ብሎ ተከታዩን ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም ክለቡ ለተጫዋቾቹ ክፍያ ያልፈፀመ መሆኑን አምኖ ነገር ግን እስከ ሰኔ 20 ድረስ ጊዜ ይሰጠኝ በማለት የጠየቀ በመሆኑና ኮሚቴው በክለቡ ላይ የተፈጠረውን ጫና በመመልከት እስከ ሰኔ 15 ድረስ የሚፈለግበትን ክፍያ እንዲፈጽም ወስኖ ተጫዋቾቹም በአፋጣኝ ሥራ ገብተው አገልግሎት እንዲሰጡ አዟል። ክለቡ በውሳኔው መሰረት ክፍያውን እንደውሳኔው ሳይፈፅም የተሰጠው ጊዜ ገደብ ካለፈበት 2% በየቀኑ ጨምሮ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡ ክፍያውን የማይፈጽም ከሆነ ግን ክለቡ ከውድድር እንደሚታገድ እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ ምንም አይነት አገልግሎት እንደማያገኝ አሳስቧል።

አቤቱታውን ያቀረቡት ተጫዋቾች ይግባኝ የማለት መብት እንዳላቸው የተጠቆመ ሲሆን ከውሳኔው በኋላ ደግሞ ክለቡ አዲስ ማስታወቂያ ማውጣቱን አውቀናል። ክለቡ ባወጣው ማስታወቂያ ላይም በስራ ገበታቸው ያልተገኙ 18 ተጫዋቾች ስማቸው ተዘርዝሮ እስከ ነገ 6 ሰዓት ባህር ዳር ሌክ ማርክ ሆቴል ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ በጥብቅ አሳስቧል።

ከነገ በስትያ 10 ሰዓት ከፋሲል ከነማ ጋር የ26ኛ ሳምንት ጨዋታውን የሚያከናውነው ቡድኑ ይህንን ዘገባ በምንሰራበት ወቅት 9 ተጫዋቾችን ይዞ ያልተሟላ ልምምዱን እያከናወነ እንደሚገኝ ተረድተናል።