የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ እና መከላከያ መካከል ተደርጎ በ0-0 ውጤት ተቋጭቷል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ሂደት ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ የዘለቀ ሲሆን በየመሀሉም ለጎል የቀረቡ አጋጣሚዎችን አይተንበታል። በተሻለ የማጥቃት ጫና ጨዋታውን የጀመሩት መከላከያዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ አቱላ ከሳጥን ውጪ ባደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ወደ ግብ መድረስ ጀምረዋል።
በሂደት ፈጠን ባለ ጥቃት ምላሽ መስጠት የጀመሩት ወልቂጤዎች በበኩላቸው የተስፋዬ ነጋሽ የግራ መስመር ሩጫዎችን መሰረት አድርገው የማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ 16ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከቀኝ መስመር ሦስት ተጫዋቾችን በማለፍ ከቅርብ ርቀት ወደ ግብ በላከው ኳስ ለግብ ቀርበው ነበር።
ጦሩ መነሻቸውን ከቢኒያም በላይ ቅብብሎች ባደረጉ ኳሶች ወልቂጤዎች ደግሞ ሰፊ የመጫወቻ ቦታ ነፃነት የነበረው አብዱልከሪም ወርቁን ያማከሉ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክረዋል። ጨዋታው ለደቂቃዎች ከጠንካራ ሙከራ ርቆ ቢቆይም በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ግብ ለማየት ተቃርበን ነበር። 35ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ አቱላ በቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ያሳለፈለትን ኳስ እስራኤል እሸቱ ጥሩ አድርጎ በግንባሩ ቢገጭም ሰዒድ ሀብታሙ በቅልጥፍና አድኖበታል። እስራኤል ከአንድ ደቂቃ በኋላም ጦሩ መሀል ለመሀል በሰነዘረው ጥቃት ከቢኒያም በላይ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውስጥ ባደረገው ደካማ ሙከራ አምክኗል።
በወልቂጤ በኩል 40ኛው ደቂቃ ላይ ጫላ ተሺታ አብዱልከሪም ወርቁ ከግራ መስመር ያደረሰውን ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ ቢገባም ነፃ ለነበረው ተስፋዬ ነጋሽ ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም በቀጥታ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ ክሌመንት ቦዬን የፈተነ አልሆነም። አጋማሹ የተቋጨውም ምንተስኖት አዳነ ከሳጥን ውጪ ባደረገው እና ወደ ላይ በተነሳ ኳስ ነበር።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው የኃይል አጨዋወት ጫን ብሎት ነበር። ሆኖም ግጭቶች ይበርኩቱ እንጂ ቡድኖቹ እንደመጀመሪያው ሁሉ ወደ ፊት ገፍተው የመጫወት ፍላጎታቸው ይታይ ነበር። በዚህ ረገድ የተሻለ የነበረው መከላከያ ሲሆን ግብ ለማስቆጠር የቀረበባቸው አጋጣሚዎችም አልጠፉም። 53ኛው ደቂቃ ላይ የአዲሱ አቱላ ሌላ የተመጠነ ኳስ ወደ ወልቂጤ ሳጥን ቢያመራም የተሾመ በላቸው የግንባር ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል። ከአንድ ደቂቃ በኋላም በሰዒድ ሀብታሙ እና ውሀቡ አዳምስ አለመግባባት ምክንያት ምንተስኖት አዳነ ጥሩ ዕድል አግኝቶ በግንባሩ ሞክሮ ወጥቶበታል።
ወልቂጤዎች የጦሩን የኳስ ንክኪዎች ወደ አደጋነት እንዳይቀየሩ በማደረጉ የተሻሻሉባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ጦሩ 62ኛው ደቂቃ ላይ በቢኒያም በላይ ያዳረገው ሙከራም ከቅጣት ምት የተገኘ ነበር። አልፎ አልፎ ብቅ የሚለው የወልቂጤዎች መልሶ ማጥቃት 68ኛው ደቂቃ ላይ ተቀያሪው ያሬድ ታደሰ በግራ የሳጥኑ ክፍል ይዞ በመግባት ባደረገው እና ወደ ውጪ በወጣው ሙከራ ለግብ መቅረብ ችሎ ነበር።
የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የጦሩ ቅብብሎች በሰራተኞቹ ሳጥን ውስጥ ዘልቀው መግባት የተቸገሩባቸው ተደጋጋሚ አስገዳጅ ቅያሪዎችን ያደረጉት ወልቂጤዎች መልሶ ማጥቃትም ከጨዋታ ውጪ እየሆንኑ የታዩባቸው ነበሩ። ወደ ጨዋታው ማብቂያ ላይ የመከላከያ ጥቃት በተለይም ተቀይሮ በገባው ሠመረ ሀፍተይ የቀኝ መስመር ሩጫዎች አደገኛ ዕድሎችን ሲፈጥር ቢታይም ተፈላጊውን ጎል ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።
በመጨረሻ ደቂቃ ወልቂጤዎች ሳጥን ውስጥ በተገኙበት አጋጣሚ ዳዊት ማሞ አቡበከር ሳኒ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል ያቀረቡት የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄ በዕለቱ አርቢትር ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። የቢኒያም በላይ የቅጣት ምት ሙከራ በሰዒድ ሀብታሙ የተመለሰበት ቅፅበትም 99 ደቂቃዎች የዘለቀው ጨዋታ የመጨረሻ ዓይን ሳቢ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ወደ 32 ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ወደ 31 ነጥቦች ከፍ ቢሉም ከወራጅ ቀጠናው የነበራቸውን ርቀት በድል ማስፋት ሳይችሉ ቀርተዋል።