ወልቂጤ ከተማ እና መከላከያ ያለ ጎል ካጠናቀቁት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኞች ስለ ጨዋታው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ
ተቀራራቢ ነጥብ ላይ ሆኖ ስለመገናኘት
“የተወሰኑ ቀናትን ነው ልምምድ የሰራነው፡፡ የተወሰነ ቀን ልምምድ ለሰራ ቡድን አቻ መጥፎ አይደለም፡፡ ልጆቻችን ግን የሰጡት ነገር ከፍተኛ ነው እና ልጆቼን ሳላደንቅ አላልፍም፡፡
18 ቀናት ልምምድ አለመስራታቸው
“በፊትነስ ደረጃ አንደኛ የምለው ቡድን መከላከያ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እኛ አልሰራንም፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ አካል ብቃት ካለው ቡድን ጋር 90 ደቂቃ በዚህ ልክ መታገል ቅድም እንዳልኩት ሳይንሱ ፉርሽ ነው፡፡
ስለ ጫላ ተሺታ የመስመር አጨዋወት
“ጫላ ምናልባት ዛሬ ፋይናል ሰርድ ላይ ያገኛቸውን ኳሶች በተወሰነ መልኩ ባለመረጋጋት አጥቷቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ሻርፕነት ዛሬ የለም ምናልባት ፣ ከጌታነህ ጋር ነው ቦክስ ውስጥ የተላመዱት ዛሬ ደግሞ አዲስ አጨዋወት ነው ይዘን የመጣነው፡፡ ይሄ ተፅእኖ የፈጠረበት ይመስለኛል ዞሮ ዞሮ ግን መጥፎ እንቅስቃሴ አይደለም ያደረገው፡፡
በሁለት የተከላካይ አማካይ ስለ መጫወታቸው
“4-2-3-1 ነው ዛሬ ለመጫወት የሞከርነው፡፡ ምክንያቱም መከላከያ ከግብ ጠባቂው አንስቶ የኋላውን መስመር ስትመለከት ያገኙትን በረጃጅም ኳስ ነው የኛን ተከላካዮች ማግኘት የሚፈልጉት ፣ ስለዚህ በቂ ሽፋን ማግኘት አለባቸው የአየር ኳስ ማሸነፍ አለብን፡፡ እዛ ጋር ስለዚህ ኤዲ እና ሀብታሙ ይሄን እንዲያደርጉ ነው፡፡ ኤዲ የአየር ኳስ እንዲያሸንፍ ቢውልድ አፕ ላይ ሀብታሙ እንዲሳተፍ ነበር። ነገር ግን በተጨማሪ ኤዲም እየተሳተፈ የተሻለ ነገር አድርገዋል፡፡
አሰልጣኝ ዮሃንስ ሣህሌ – መከላከያ
ስለ አጨራረስ ችግር
“የእኛ ሀገር ጨዋታ እንዲህ ሲቆራረጥ ተጫዋቾች ላይ ትሰራለህ ፣ ትለፋ ትለፋ እና ሀያ ቀን ምናምን ሄደህ ስትመጣ ደግሞ ከዜሮ ትጀምራለህ፡፡ ዛሬ ለምሳሌ ያጣነው ምንድነው መጨረስ የሚለውን ነገር ነው፡፡ ሻርፕ መሆን የሚመጣው በተደጋጋሚ ስትጫወት ነው፡፡ ስለዚህ የሳትናቸው ኳሶች ከውድድር ውጪ ሆኖ ከመምጣት ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ይሄ የአዕምሮ ፍጥነት ውሳኔዎች ላይ የጉልበት ፣ የጥንካሬ ፣ የአካል ብቃት ብቻ አይደለም፡፡የምትወስናቸው ውሳኔዎች አዕምሮ ላይ ላሽቀው እዚህ ሜዳ ላይ ስትመጣ ችግር ውስጥ ትገባለህ እነኚህ ነገሮች ናቸው ዛሬ ያጋጠሙን በትንፋሻችን ጥሩ ነን ፣ በማጥቃት ጥሩ ነን ፣ በፍላጎት ጥሩ ነን ፣ ወደ ፊት በመሄድ ጥሩ ነን፡፡ እነኚህ ሁላ በጎል ካልታጀቡ ይሄ ደግሞ የሚመጣው በምንድነው ከአዕምሮ ጋር ነው፡፡ ኳሶች ይመታሉ ወደ ጎል በረኛ ይይዘዋል ይመታሉ በረኛ ያወጣዋል፡፡ ይሄ ማለት በአዕምሮ የምትወስናቸው የመጨረሻ ውሳኔዎችህ ሻርፕ አይደሉም፡፡
ስለ ተጋጣሚ ወልቂጤ ከተማ
” አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት የሚችሉት ሁሉ ሞክረዋል፡፡ በመውደቅም ጊዜ በማቃጠልም ፣ ስለ ዳኛ ማውራት ባልፈልግም አንዳንድ ነገሮችን ማንበብ መቻል አለብህ፡፡ ስንት ፋውሎች ተሰርቶ ስንት ቢጫ ተሰጠ ? ዛሬ በእጅ ተነክቶ ቢጫ የለም ከኋላ ተምቶ (ህጉ የሚለውን ነው) እንደገና አትጠይቅ ይሉሀል፡፡ በቴሌቪዥን በሌላው ዓለም የምናየው መሳደብ ልክ አይደለም ፣ ዳኛውን ማዋረድ ልክ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ትንሽ እንደ ባለስልጣን ሳይሆን እንደ ኳስ እናድርገው መጠየቅም ጥሩ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ወልቂጤ የፈለገውን ይዞ ወጥቷል በእኛ በኩል በአጨራረስ ካልሆነ በስተቀር በፍላጎት ጥሩ ነበርን፡፡