አዲስ አበባ ከተማ ስለሚገኝበት ሁኔታ አጣርተናል

ነገ ቀትር ላይ ወላይታ ድቻን የሚገጥመው አዲስ አበባ ከተማ አምስት ቀናትን ያለ ልምምድ አሳልፎ ነገ ጨዋታውን ያከናውን ይሆን ?

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከታችኛው የሊግ ዕርከን በማደግ በሊጉ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው የመዲናይቱ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ ዓመቱን ሲጀመር በተሻለ የውጤት ጎዳና ላይ መጓዝ ቢችልም በሂደት ግን ወደ ውጤት ዕጦን ውስጥ እየገባ በመጨረሻም በወራጅ ቀጠናው ላይ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡ የዓመቱ ሦስተኛ የክለቡ አሰልጣኝ ሆነው በተሾሙት ጳውሎስ ጌታቸው መሪነት በባህርዳር ስታዲየም ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች መልስ ነገ ቀትር ላይ 7፡00 ላይ ወላይታ ድቻን በ26ኛ ሳምንት ጨዋታ የሚገጥመው አዲስ አበባ ከተማ ያለፉትን አምስት ቀናት ልምምድ ሳይሰራ መሰንበቱ ሲያነጋግር ቆይቷል።

የክለቡ ሰላሳ የሚጠጉ ተጫዋቾች ባሳለፉነው ዕርብ “የሁለት ወር ከአስር ቀናት ደመወዝ አልተከፈለንም” በማለት ለክለቡ የቦርድ አካላት ፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፣ ለፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር በደብዳቤ በመፈራረም ልምምድ ማቆማቸውንም በመጠቆም ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ የቡድኑ ተጫዋቾች ጥያቄያቸው ባለመመለሱ ዛሬን ጨምሮ ላለፉት አምስት ቀናት ከልምምድ ርቀው ቆይተዋል፡፡ በባህርዳር ወተር ፍሮንት ሆቴል የሚገኙት የቡድኑ ተጫዋቾች እንደሚሉት “ማንም መጥቶ የሚያናግረን ባለመኖሩ እና ችግሩን ሊፈታ የተዘጋጀ አካል ስለሌለ ልምምድ አሁንም እየሰራን አንገኝም” ሲሉ ሀሳባቸውን ያካፈሉን ሲሆን ፣ ሶከር ኢትዮጵያም የክለቡን ስራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ታከለን አናግራለች ስራ አስኪያጁም ክለቡ ነገ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ “የሚያስፈልጋቸውን ለመፈፀም ዝግጁ ነን፡፡ የጠየቁት ተሟልቶላቸው ነገ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ የእነርሱን ጥያቄ ለመመለስ የባንክ ጉዳዮችን በመጨረስ ላይ ነን፡፡ አሁን መናገር ባልፈልግም ቡድኑን ማትረፍ ከቻሉ ታይቶ የማይታወቅ ነገር ይጠብቃቸዋል”፡፡ ሲሉ ነግረውናል፡፡

በሌላ በኩል ከአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ባገኘነው መረጃ መሰረት ተጫዋቾቹ በግላቸው ሲዘጋጁ መቆየታቸውን እና የነገውን ጨዋታ እንደሚያከናውኑ ነግረውናል።