የአሠልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 2-1 አዳማ ከተማ

ኢትዮጵያ ቡና ከመመራት ተነስቶ አዳማ ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል።

ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው…?

ጥሩ ነበር። በጫና ውስጥ ሂደቱን ለማስቀጠል የነበረ ግብ ግብ ነበር። እነርሱ ጫና ፈጥረው ሂደት ውስጥ እንዳንቆይ የማድረግ ነገር ነበረባቸው እኛ ደግሞ ሂደቱ ውስጥ ለመቆየት ነበር የፈለግነው። በእረፍትም በሂደቱ ውስጥ ለመቆየት ምን ማድረግ አለብን ብለን ነበር ያሰብነው።

ከተጋጣሚ ስለገጠማቸው አጨዋወት…?

በከፍተኛ ሀይል የሚጫወት ቡድን የተወሰኑ ደቂቃዎች ነው የሚቀጥለው። 90 ደቂቃ በዛ ደረጃ ሊጫወት አይችልም። አንደኛም ተጫዋቾቹ ይሄን ግንዛቤ እንዲያገኙ ነበር ያደረግነው። ነገሮች እየተፈቱ እንደሚሄዱ። ሁለተኛ ደግሞ ከአጠቃቀም አንፃር ከጫናው ለማምለጥ ማንን መጠቀም አለብን የሚለውን ነገር ነበር ለተጫዋቾቹ ለማሳየት የፈለግነው። በዚህ ውስጥ ሂደቶቹ ይቀጥሉ ነበር። የሚቋረጡም ኳሶች ነበሩ። ግን መፍትሔው እስካለ ድረስ ያንን ነበር ስናደርግ የነበረው።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው ስለመጡበት ምክንያት…?

በመጀመሪያው አጋማሽም ጥሩ ነበር። አንድ በባህሪ ቡድኖች ሁል ጊዜ ግብ ካገቡ በኋላ የማፈግፈግ እና ያንን ጎል የመጠበቅ ነገር አለባቸው። ይሄ በተወሰነ ደረጃ ጠቅሞናል ብዬ አስባለው። ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ጫና ፈጥረው ተጫማሪ ጎል ለማስቆጠር ሊፈልጉ ስለሚችሉ ጥንቃቄ እየወሰድን ቅርፃችንን ጠብቀን ሳንዝረከረክ እስከ መጨረሻው ለመጫወት ሞክረናል።

ስለአቡበከር ናስር ብቃት…?

አቡበከር ያለው የግል ብቃት እየታየ ነው። ሁል ጊዜ ሜዳ ውስጥ በሚያደርገው ነገር በከፍተኛ ሁኔታ ቡድኑን እየጠቀመ ነው። እየታየ ነው።

ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ

ጨዋታው እንዴት ነበር…?

እንደታየው ለመጫወት ባሰብነው መልኩ መጀመሪያ ላይ ለመጫወት ሞክረናል። ከዛ በኋላ ግን የተሳቱት ኳሶች ዋጋ አስከፍሎናል። ከእረፍት በፊት ብንጨርሳቸው ጥሩ ነበር። ግን አለመሆኑ ዋጋ አስከፍሎናኔን። ይሄም ቢሆን ግን ችግር የለውም የሚሻሻል ነገር ነው።

ተጋጣሚን ያማከለው አጨዋወታቸው ያልቀጠለበት ምክንያት…?

ቡናዎች ወደ መሐል ሜዳ ሲደርሱ ነበር ኳሱን ለመንጠቅ ያሰብነው። ይሄንን ነገር በተወሰነ መልኩ ለማስቀጠል ሞከርንና ወደ ራሳችን ሜዳ አፈገፈግን። ይሄ ደግሞ ዋጋ አስከፍሎናል።

ቡድኑ ላይ ስለነበረው ስህተት….?

የሚታይ ነገር ነው። እነዛ ያገኘናቸው አጋጣሚዎች ሄደዋል። ተጫዋቾቹ ግን ትንሽ መጓጓት ይታይባቸዋል። ለማግባት ያላቸው ነገር አጋሮቻቸውን የማየት ነገር ቀንሶታል። በጣም ጉጉ ነበሩ። አብዲሳም ሆነ አሜ ያገኟቸው ኳሶች ቢያልቁ ውጤቱ ይህ ላይሆን ይችላል። ይሄ ነገርግን የሚመጣው ከጉጉት እና ለቡድኑ አንድ ነገር ለማድረግ ከመፈለጋቸው የተነሳ ነው።

ስለቀጣይ ጨዋታዎች…?

30 ነጥብ ላይ ነን። የታችኛውን ቦታ ግን ፈፅሞ አናስበውም። ትላልቅ ጨዋታዎች ይቀሩናል። ግን እነዛን ተወተን የተሻለ ደረጃ ላይ ሆነን እንጨርሳለን።