ሪፖርት | ሀዋሳ በብሩክ እና ኤፍሬም አስገራሚ ጥምረት ታግዞ ድሬን ረቷል

ሀይቆቹ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከብርቱካናማዎቹ ሦስት ነጥብ ሸምተዋል።

ቀጥተኛ አጨዋወት ለመከተል ሲጥሩ የታዩት ሁለቱ ቡድኖች እምብዛም ኳስ ለማንሸራሸር ፍላጎት ሲያሳዩ አልተስተዋለም። ይልቁንም ረጃጅም ኳሶችን በማዘውተር ወደ ግብ ለመድረስ ሲታትሩ ነበር። በዚህ ሂደት የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ በ9ኛው ደቂቃ ተስተናግዷል። በተጠቀሰው ደቂቃ በግራ መስመር ወደ ሀዋሳ የመከላከል ወረዳ ያመሩት ድሬዳዋዎች ሔኖል አየለ በግንባሩ በሞከረው ኳስ ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። ከአስር ደቂቃዎች በኋላም ቡድኑ በአብዱረህማን ሙባረክ አማካኝነት ሌላ ጥቃት ሰንዝሮ ተመልሷል።

ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሰጡ የሚመስሉት ሀዋሳዎች በ20ኛው ደቂቃ ለግብ የቀረቡበትን ሁነት ከመዓዘን ምት ቢያገኙም እርጋታ እና መናበብ እርቋቸው ግልፁን ዕድል አምክነውታል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ግን የድሬዳዋን ተከላካዮች የወረደ አደረጃጀት ተጠቅመው ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም በመስመሮች መካከል የተገኘው ብሩክ በየነ በቀኝ መስመር ራሱን ነፃ አድርጎ እየሮጠ ለነበረው ኤፍሬም አሻሞ አቀብሎት ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ኳሱን ከድር ኸይረዲን ሰውነት ላይ በማንጠር ከመረብ ጋር አዋህዶታል።

በእንቅስቃሴ ደረጃ በአንፃራዊነት የተሻሉት ብርቱካናማዎቹ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢሞክሩም ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ይባስ በ40ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ቡድኑ ለማጥቃት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ የላከውን ኳስ ያቋረጡት ሀዋሳዎች በጥሩ ሁኔታ መስርተውት ሳጥን ውስጥ ገብተው የመጨረሻ ኳስ የደረሰው ወንድማገኝ ኃይሉ ወርቃማውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አጋማሹ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃም በቃሉ ገነነ ሌላ ሙከራ ልኮ ወጥቶበታል።

ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በአንደኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ተፈጥሯል። በዚህም መሪ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት ሀዋሳዎች ከተከላካይ ጀርባ የሚገኘውን ጥልቀት በማጥቃት ሁለተኛ ግብ ሊያገኙ ነበር። ነገርግን ፍጥነቱን ተጠቅሞ ኳሱን በማግኘት ግብ ጠባቂው ደረጄ ዓለሙን ያለፈው ብሩክ ሁለተኛ ግብ እንዲያስቆጥር ለኤፍሬም የላከውን ኳስ ከድር እና አብዱለጢፍ ተረባርበው ከግቡ መስመር አውጥተውታል።

አጀማመራቸው ጥሩ የነበረው ሀዋሳ በ46ኛው ደቂቃ ያገኙትን ዕድል በአስቆጪ ሁኔታ ቢያመክኑትም ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ሁለተኛ ጎል አግኝተዋል። ቀድመን በጠቀስነው ደቂቃ ዕድሉን የፈጠረው ብሩክ በ51ኛው ደቂቃ ከዳንኤል ደርቤ የደረሰውን ኳስ በግራ እግሩ መረብ ላይ አስቀምጦታል። ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ እየወጣባቸው የመጣው ድሬዎች በደቂቃዎች ልዩነት አብዱለጢፍ መሐመድ ከመስመር አሻምቶት ሔኖክ አየለ ለመጠቀም በጣረው ጥሩ ኳስ ወደ ጨዋታው ሊመለሱ ነበር። በ63ኛው ደቂቃም ይሁ አጥቂ ተቀይሮ ከገባው አቤል ከበደ የደራውን የዐየር ኳስ በግንባሩ ወደ ጎልነት ሊቀይር ነበር።

ድሬዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በሚጥሩበት ሰዓት ከኋላቸው ሰፊ ቦታን ትተው እየሄዱ ራሳቸውን ለጥቃት ጋብዘዋል። በ66ኛው ደቂቃም የቀደሙት ሁለቱ ግቦች ላይ ስማቸውን ያስቀመጡት ብሩክ እና ኤፍሬም ዳግም ተጣምረው ብሩክ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። በጨዋታው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ 88 ደቂቃዎችን መጠበቅ ግድ ያላቸው ድሬዎች በጭማሪው ደቂቃ በሔኖክ አማካኝነት የማስተዛዘኛ ጎል አግኝተው ጨዋታውን በሽንፈት አጠናቀዋል።

ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር የተገናኘው ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 39 አድርሶ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሦስት ነጥብ ያስረከበው ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ (29) እና ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ ተቀምጧል።

ያጋሩ