የጨዋታ ሳምንቱ ነገ የሚጠናቀቅባቸውን ሁለት ግጥሚያዎች በዳሰሳችን ተመልክተናል።
ጅማ አባ ጅፋር ከ ሀዲያ ሆሳዕና
ሊጉ ወደ ፍፃሜው እየቀረበ ሲሄድ ለአንዱ ተጋጣሚ ከፍ ያለ ትርጉም ያላቸው ጨዋታዎች መኖራቸው የማይቀር ሲሆን የነገ ረፋዱ ጨዋታም ከዚህ ውስጥ የሚመደብ ነው። ከአደጋ ዞኑ የመውጫ በር በዘጠኝ ነጥቦች ወደ ኋላ ርቆ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ከዚህ ጨዋታ ከሙሉ ውጤት ያነሰ ነጥብ ማግኘት ወደ ከፍተኛ ሊጉ የሚያቀርበው በመሆኑ እጅግ ውሳኝ ጨዋታ እንደሚያደርግ ይታሰባል። በአንፃሩ የሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና አሰተማማኝ የነጥብ ርቀት ላይ ባይገኝም ይበልጥ ደረጃውን ለማሻሻል እና ከስጋት ሙሉ ለሙሉ ለመራቅ የሚጠቅመውን ጨዋታ ያደርጋል።
ግንቦት 27 ወደ ልምምድ የተመለሱት ጅማዎች ከመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎቻቸው አንድ ነጥብ ብቻ እንደማሳካታቸው የዕረፍት ጊዜው የመጨረሻ ትንፋሻቻውን ሰብስበው በሙሉ ኃይል ነጥቦችን ለመሰብሰብ እንደሚረዳቸው ይገመታል። ወትሮውንም ካለበት ደረጃ በተለየ መልኩ ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አቀራረብ ያለው ቡድኑ ነገም በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርቶ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀስ ይጠበቃል። በአንፃሩ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ካሉ ቡድኖች ጋር ጥሩ ሪከርድ የሌለው ሀዲያ ሆሳዕና በቀጥተኛ ፈጣን ጥቃቶች ከጅማዎች ውጤት ፈላጊነት መነሻነት ከኋላ ሊኖር የሚችለውን ክፍተት የመጠቀም ዕድል ይኖረዋል። ተስፋዬ አለባቸውን በጉዳት ፍሬዘር ካሳን በቅጣት የሚያጣው ቡድኑ በተለይም የተከላካይ አማካዩ አለመኖር በድሬዳዋው ጨዋታ ላይ የፈጠረበትን ዓይነት ክፍተት ከተወ በጅማ አማካዮች መሀል ሜዳ ላይ በቀላሉ ብልጫ ሊወሰድበት እንደሚችል ይገመታል። በጅማ በኩል ቅጣት ላይ የሚገኘው አላዛር ማርቆስ እና ቡድኑን ያልተቀላቀለው ሽመልስ ተገኝ ለነገው ጨዋታ እንደማይደርሱ ተሰምቷል።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ ፣ ረዳቶች ትግል ግዛው እና ወጋየሁ አየለ ፣ አራተኛ ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ
ተጨማሪ ዳኞች – ዳንኤል ጥበቡ እና ለአለም ዋሲሁን
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ዓምና እና ዘንድሮ በሦስት ጨዋታዎች የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ነጥብ ተጋርተው የማያውቁ ሲሆን ስድስት ግቦች ያሉት ሀዲያ ሆሳዕና ሁለቴ አራት ግቦች ያሉት ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ አንዴ ድል ቀንቷቸዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
ለይኩን ነጋሽ
በላይ አባይነህ – ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ተስፋዬ – ወንድማገኝ ማርቆስ
ሱራፌል ዐወል – መስዑድ መሐመድ – ዳዊት እስቲፋኖስ
ዱላ ሙላቱ – መሐመድኑር ናስር – እዮብ አለማየሁ
ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)
መሳይ አያኖ
ብርሃኑ በቀለ – ግርማ በቀለ – ቃለአብ ውብሸት – እያሱ ታምሩ
ኤፍሬም ዘካሪያስ – ሳምሶን ጥላሁን – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን
ሚካኤል ጆርጅ – ሀብታሙ ታደሠ – ራምኬል ሎክ
ሰበታ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
26ኛው ሳምንት በሁለት ፅንፍ የሚገኙ ቡድኖችን በማገናኘት ይቋጫል። በሁለት ተከታታይ ድሎች ተነቃቅቶ የነበረው ሰበታ በአዳማ ከተማ ሰፊ ሽንፈት አስተናግዶ ነበር ወደ ዕረፍቱ ያመራው። በመሆኑም በሊጉ ለመቆየት የመጨረሻ ፈተናውን በነገው ከባድ ጨዋታ ይጀምራል። በአንፃሩ ፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ከጣለ በኋላ የሚያደርገውን የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ልዩነቱን ወደ ሦስት ነጥብ ዝቅ ማድረግ የሚችልበትን ዕድል ይዞለት የሚመጣ በመሆኑ እጅግ ወሳኝ ይሆንለታል።
ይህንን ጨቃታ ወረቀት ላይ አይቶ የማሸነፍ ዕድሉን ለፋሲል ከነማ መስጠት የሚያስገርም አይሆንም። ለዚህ ዋና ምክንያት የሚሆነው ከሚገኙበት ደረጃ ብቻም ሳይሆን የሰበታ ከተማ የፋይናንስ ችግር ተጫዋቾችን ከልምምድ አርቆ የመቆየቱ ጉዳይ ነው። ቡድኑ ከሰባት ተጫዋቾች በላይ በልምምድ ላይ ማሳተፍ ካለመቻሉ ባለፈ አመዛኞቹ ተጫዋቾችን የሚያገኘው ከነገው ጨዋታ በፊት መሆኑ አስገራሚ ሆኗል። በእርግጥ አዲስ አበባ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ በተመሳሳይ የተጫዋቾች አድማ ላይ አሳልፈው ሜዳ ላይ ግን ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር ያደረጉት ፉክክር ለሰበታ ትምህርት የሚሆን ይመስላል።
ፋሲል ከነማ የዓመቱን እጅግ ወሳኝ ድል በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ካስመዘገበ በኋላ ውድድሩ መቋረጡ ከነበረበት የተከታታይ ድል ግለት ሊያቀዘቅዘቅ ቢችልም የፈረሰኞቹ ነጥብ መጣል ደግሞ የራሱን ተነሳሽነት ይዞለት እንደሚመጣ ይጠበቃል። ዐፄዎቹ በማላዊው ጨዋታ መጠነኛ ጉዳት ገጥሞት ከነበረው ሱራፌል ዳኛቸው ውጪ የሚያጡት ተጫዋች የሌለ ሲሆን ቡድኑ ከግንቦት 21 ጀምሮ በልምምድ ላይ ቆይቷል። በነገውም ጨዋት በተለመደው ማጥቃት ላይ በተመሰረተ አጨዋወት ደጋግሞ ጥቃት በመሰንዘር ላይ የተመረኮዘ የጨዋታ ዕቅድ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ፣ ረዳቶች ሸዋንግዛው ተባበል እና ሙሉነህ በዳዳ ፣ አራተኛ ዳኛ ሄኖክ አክሊሉ
ተጨማሪ ዳኞች – ዘሪሁን ኪዳኔ እና ዳንኤል ጥበቡ
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ነገ በሊጉ ለአራተኛ ጊዜ የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ሁለት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ ፋሲል ከነማ የዘንድሮውን ጨዋታ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ፋሲል አራት ሰበታ ደግሞ አንድ ግብ አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)
ለዓለም ብርሀኑ
ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
በኃይሉ ግርማ – ጋብርኤል አህመድ
ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ዱሬሳ ሹቢሳ
ዴሪክ ኒስባምቢ
ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)
ሚኬል ሳማኪ
ዓለምብርሃን ይግዛው – ያሬድ ባየህ – ሙጂብ ቃሲም – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው
ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ – በረከት ደስታ
ኦኪኪ አፎላቢ