ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር አለሁ እያለ ነው

በወራጅ ቀጠናው እየዳከሩ የሚገኙት ጅማ አባ ጅፋሮች በዳዊት እስጢፋኖስ ድንቅ የቅጣት ምት ጎል ሀዲያ ሆሳዕናን በመርታት በሊጉ ለመትረፍ የመጨረሻ ጥረታቸውን ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

በጨዋታ ገና ከጅምሩ ኳስ በመቆጣጠር ለመጫወት ጥረት በማድረግ የጀመሩት ጅማ አባጅፋሮች የጨዋታው የመጀመሪያ አደገኛ ሙከራ ማድረግ ችለዋል ፤ 5ኛው ደቂቃ ላይ አስጨናቂ ፀጋዬ ካቋረጠው ኳስ የተገኘችውን ኳስ መስዑድ መሀመድ የመሳይ አያኖ ግቡን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ከርቀት ያደረገውን ሙከራ መሳይ እንደምንም ወደ ኃላ ሸሽቶ አድኖበታል።

በሂደት የተወሰደባቸውን ብልጫ በመቀልበስ በጨዋታው የተሻለ መንቀሳቀስ የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በተሻለ ኳሱን በማንሸራሸር እድሎችን መፍጠር ጀምረዋል በተለይም ደግሞ ከቀኝ መስመር መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶች ለማጥቃት ሙከራ አድርገዋል ፤ በዚህም በ13ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻማ ኳስ ዑመድ ዑኩሪ የመጀመሪያ ኳስ በማሸነፍ የፈጠረለትን እድል ተጠቅሞ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ከሳጥን ውጭ ያደረገውን አስገራሚ ሙከራ አላዛር ማርቆስ በግሩም ሁኔታ ሲያድንበት በ20ኛው ደቂቃ እንዲሁ ሀብታሙ ታደሰ ከተከላካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ባዬ ገዛኸኝ አንድ ተከላካይ ቀንሶ ያደረገውን ግሩም ኳስ በተመሳሳይ አላዛር ሊያድንበት ችሏል።

ጅማዎች ምንም እንኳን ብልጫ የተወሰደባቸው ቢመስልም በሂደት በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎችእንደ መጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁሉ መሀል ለመሀል የሚደረጉ ጥቃቶችን በመሰንዘር የተሻለ ለመንቀሳቀስ እና እድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል ፤ 23ኛው ደቂቃ ላይ አስጨናቂ ፀጋዬ በረጅሙ የላከውን ኳስ ግርማ በቀለ እመልሳለሁ ብሎ የገጨው ኳስ ሳይጠበቅ ወደ ግብ ቢያመራም ኳሷን መሳይ በግሩም ቅልጥፍና ያመከነበት ሲሆን በ35ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ መላኩ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ እዮብ አለማየሁ ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ በተመሳሳይ በመሳይ አድኖበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ዑመድ ዑኩሪ ከሳጥን ውጭ ባደረጋት ጠንካራ ምት ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ሀዲያዎች በ52ኛው ደቂቃ ግን ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል ፤ ተስፋዬ መላኩ ላይ በሳጥን ጠርዝ አካባቢ በተሰራ ጥፋት ጅማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ዳዊት እስጢፋኖስ በቀላሉ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች ሀዲያ ሆሳዕናዎች ምንም እንኳን ግለሰባዊ ለውጦችን በማድረግ ይበልጥ ማጥቃታቸውን ለማነቃቃት ጥረት ቢያደርጉም የነበራቸው የማጥቃት አፈፃፀም ደካማ የሚባል ነበር ፤ ከግቧ በኃላ በነበረው ሂደት በ68ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ከሳጥን ውጭ ያደረገው እና አላዛር ማርቆስ የመለሰበት አጋጣሚ እስኪፈጠር ድረስ በርከት ያሉ ደቂቃ ለመጠበቅ ተገደዋል።

ደቂቃዎች እየገፉ መሄዳቸውን ተከትሎ ጅማ አባ ጅፋሮች ይበልጥ ወደ ኃላ ሸሽተው በጥንቃቄ ለመከላከል ጥረት ያደረጉት ጅማዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል በዚህም ተጋጣሚያቸው ግልፅ እድል እንዳይፈጥር ማድረግ ችለዋል ፤ በእነዚሁ ደቂቃዎች ሀዲያ ከመስመር ከሚሻገሩ ኳሶች ባለፈ ይህ ነው የሚባል አጋጣሚ ለመፍጠር ተቸግረዋል።

በ84ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተነሳን የማጥቃት ሂደት በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቀንሶ ባዬ ገዛኸኝ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ እና በግቡ ቋሚ የተመለሰችበት አጋጣሚ ሀዲያዎች አቻ ለመሆን የቀረቡበት አጋጣሚ ነበር።

ጨዋታው በጅማ አባ ጅፋሮች ድል መጠናቀቁን ተከትሎ ነጥባቸው ወደ 23 በማሳደግ በነበሩበት 15ኛ ደረጃ ሲቀጥሉ ተሸናፊዎቹ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ በ33 ነጥብ ወደ 8ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።