የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 1-0 ሀድያ ሆሳዕና 

በጅማ አባ ጅፋር አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የረፋዱ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ የሱፍ ዒሊ – ጅማ አባ ጅፋር

ሀድያን በአመቱ ሁለት ጊዜ ስለ ማሸነፍቸው….?

“ሀድያ ሆሳዕና ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ በዚህ ውድድር ሁሉም ሜዳ ላይ ሲገባ ጠንካራ ነው፡፡ ሊወርድ ያለውም ለዋንጫ የሚጫወተውም ሁሉም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በሆነ ነገር ተበላልጠህ ነው የምትሸነፈው። ስለዚህ ጥሩ ቡድን ነው፡፡ ከመስመር በሚነሱት ላይ ነው ዛሬ ትኩረት አድርገን ስንጫወት የነበርነው፡፡ ከዚህ በፊት ከምንጫወተው በሶስት አጥቂ ብዙም አንመጣም ነበር። አሁን ግን እየተከላከሉ እያገዙ ኳስን እያንሸራሸሩ ነበር ሲጫወቱ የነበረው፡፡”

ስለ መስመር አጨዋወት…?

“እንዳሰብኩት ነው። አብዛኛውን እነ መስዑድ እና ዳዊት ኳስ ይዘው ስለሚጫወቱ ወደ መስመር ተጠግተው እንዲጫወቱ ነው፡፡ ከመስመር ላይ ብዙ እንዳይፈጥኑ ኳስ እየተጫወቱ እንዲሄዱ ነው ያሰብነው። ይሄንን አሳክተውልኛል፡፡”

ስለ ተስፋዬ መላኩ ሚና…?

“ለእርሱ ወደ ፊት እንዲሄድ ፈቅደንለታል። በ4-3-3 ስንጫወት ሶስቱ ተከላካዮች ብዙ አይመጡም እርሱ ግን ብዙ እየመጣ እንዲጫወት ሚና ሰጥተነው ነበር። ይሄም ጥቅም አስገኝቶልናል፡፡ ብዙ በማጥቃቱ ሳይሆን ኳሱን በማንሸራሸር መጫወት ላይ ብዙ አግዞናል ይመጣል ፤ ይጫወታል። አንቸገርም ነበር ኳስን ለመቀባበል፡፡”

ቡድኑ በሊጉ ስለ መቆየት ተስፋው…?

“ያለውን በጥሩ ሁኔታ ከፈጣሪ ጋር እያደረግን መጨረሻውን ማየት ነው፡፡ በእርግጥ ጨዋታዎች አጥረዋል፡፡ አሸንፈህም የሌላውን መሸነፍ ትጠብቃለህ። ያለህን ጨዋታ እያሸነፍክ መጨረሻውን ማየት ነው፡፡”

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀድያ ሆሳዕና

በጅማ አባ ጅፋር በደርሶ መልስ ስለገጠማቸው ሽንፈት…?

“በእርግጥ በእግር ኳስ ከባዱ ነገር ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው። ትንሽ ያስቸግራል፡፡ መጀመሪያም ስጋቴን ተናግሪያለሁ፡፡ ወጣት እና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ኳስን የሚችሉ ስላሉ እንደምንቸገር አምነን ነበር፡፡ እኛም በእዛ ልክ ተዘጋጅተን ነበር የመጣነው። አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ አንድ ለባዶ ተሸንፈናል፡፡ የእግር ኳስ አንዱ ባህሪ ስለሆነ ተቀብለናል፡፡”

በቡድኑ ውስጥ የነበረው ክፍተት…?

“ትክክል ያልነበረ ነገር አለ ብዬ የማምነው ጉጉት ነው። ወይም የምንሰጣቸው ግምቶች የተሳሳቱ ሊሆኑ ይችላል ብዬ ስለማስብ እንጂ ሌላ የጎላ ነገር አላየውባቸውም፡፡ ተጫዋቾቼ ላይ ስጋቴም እሱ ነበር። ለቀጣዮቹ ጨዋታዎች እነዚህን አስተካክለን እንመጣለን፡፡”

ስለ አጨራረስ ችግር…?

“እሱ ትልቁ ነገር ነው፡፡ አጥቂዎች አግኝተዋል ፤ ሞክረዋል ማግባት ነው የሚቀረን። ትልቁ ነገር እዛ ጋር መድረሳችን ነው፡፡ ቀጣይ ላይ ደግሞ አግብተን ለማሸነፍ የምንሰራበትን የአጨራረስ ስራን ጨምረን ለቀጣዩ መዘጋጀት ነው ያለን አማራጭ፡፡”

ላለመውረድ ስለሚደረገው ፉክክር…?

“ፉክክሩ ከባድ እየሆነ ነው የመጣው፡፡ በጣም ከባድ ነው ማለት ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ ከላይም ከታችም ወጠር ብሏል፡፡ ሁሉም አሰልጣኞች ላይ ከባድ ጫና ይኖረዋል ብዬ ነው የማስበው፡፡ እኔ ግን በግሌ የምለው ጫናዎቹን መቋቋም ስለምንችል ሁላችንም የሚገባንን ነገር ሜዳ ላይ ይዞ መገኘት ብቻ ነው። ከመጨነቁ በላይ ትልቁ እዛ ላይ ብንሰራም የተሻለ ነው፡፡”