ሪፖርት | ፋሲል ከሰበታ ሦስት ነጥብ በመሸመት ከመሪው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሦስት አጥብቧል

ፋሲል ከነማ በአምበሉ ያሬድ ባየህ ብቸኛ ግብ ሰበታ ከተማን በመርታት የዋንጫውን ፉክክር ከፍ አድርጓል።

ሁለት ለየቅል የሚገኙ ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ በ4ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ሙከራ ተደርጎበታል። ከደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጋር በተገናኘ በተፈጠረ ቅሬታ አብዛኞቹን ተጫዋቾች ሳይዝ ዝግጅቱን ሲያደርግ የነበረው ሰበታ ከተማ ዛሬ ረፋድ እና ቀትር ባገኛቸው ተጫዋቾች ጨዋታውን እየከወነ ቢገኘም በተጠቀሰው ደቂቃ በአንተነህ ናደው አማካኝነት የመጀመሪያ ጥቃት ሰንዝሯል። በተቃራኒው ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው ሲጫወቱ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በዋነኛነት የመስመር ላይ ሩጫዎችን በማዘውተር ጥቃት መዘንዘር ይዘዋል። በተለይ በ21ኛው ደቂቃ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ወደ መስመር አጋድሎ ሲጫወት የነበረው ኦኪኪ አፎላቢ ያሻገረውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግንባሩ ለመጠቀም ጥሮ የመሐል ተከላካዩ ወልደአማኑኤል ጌቱ እንደምንም ታግሎ ያወጣበት አጋጣሚ መሪ የሚሆኑበት ነበር።

ፋሲል ከነማዎች ኳሱን በተሻለ ሁኔታ ቢቆጣጠሩም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ዓላማ ቢስ ነበሩ። ቡድኑም ከእጥፍ የበለጠ የቅብብል ቁጥር ቢያስመዘግብም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ 32 ደቂቃዎችን መጠበቅ አስፈልጎታል። በተጠቀሰው ደቂቃም ሽመክት ጉግሳ ከበዛብህ መለዮ የተረከበውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ልኮት የግብ ዘቡ ሰለሞን ደምሴ ተቆጣጥሮታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ግን የመዓዘን ምትን መነሻ ካደረገ ኳስ ፍሬያማ ሆነዋል። በዚህም ሽመክት ያሻማው የመዓዘን ምት ተገጫጭቶ ዳግም ደርሶት ወደ ሳጥን ሲልከው ቢያድግልኝ ጨርፎት በሩቁ ቋሚ ለነበረው ያሬድ ባየህ ደርሶ አምበሉ በግራ እግሩ ግብ አድርጎታል።

ግቡ ከተቆጠረባቸው በኋላም የአጨዋወት ለውጥ ያላደረጉት ሰበታዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ወርደው በመጫወት በመልሶ ማጥቃቶች እና ረጃጅም ኳሶች ብቻ ዕድሎችን ለመፍጠር አስበዋል። በ40ኛው ደቂቃም ቢስማክ አፒያ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረው ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃም አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ሌላ ድንቅ ሙከራ በግራ እግሩ አድርጎ የግቡ አግዳሚ ከግብነት አግዶበታል።

ምንም እንኳን ውጤታማ ባይሆኑም በእንቅስቃሴ ደረጃ የመጀመሪያውን አጋማሽ በጥሩ ሁኔታ የፈፀሙት ሰበታዎች ሁለተኛውንም አጋማሽ በተሻለ ልዕልና ጀምረው አቻ ሊሆኑ ተቃርበው ነበር። በዚህም ገና የዳኛው ፊሽካ በተነፋ በሰከንዶች ውስጥ ቢስማክ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ግብ ለማስቆጠር ከጫፍ ደርሶ ነበር። በተቃራኒው ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት መሪዎቹ በ60ኛው ደቂቃ በኦኪኪ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል ሊያገኙ ነበር። በተጨማሪም ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ የቡድኑን መሪነት ሊያሳድግ ጥሮ መክኖበታል።

እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ሰበታዎች ደቂቃ በደቂቃ እየወረዱ መጥተዋል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሲያደርጉት የነበረው ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችም ተቀዛቅዘው ታይተዋል። ይባስ በ75 እና 77ኛው ደቂቃ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። በመጀመሪያ ኦኪኪ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ተገኝቶ ሲሞክር በመቀጠል ደቂቃ ናትናኤል በተቃራኒ አቅጣጫ ተገኝቶ የቡድኑን አምስተኛ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሰንዝሯል። ነገርግን ሁለቱንም ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎች ግብ ጠባቂው ሰለሞን አምክኗቸዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ እና በረከት ደስታ ሌሎች ሙከራዎችን ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።

በውጤቱ መሰረት ዐፄዎቹ ነጥባቸውን 52 በማድረስ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ ሦስት አጥበዋል። ሰበታ ከተማዎች ደግሞ በ20 ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ፀንተው ተቀምጠዋል።