ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተበልጣ የተረታቸው ግብፅ የቡድኗን አሰልጣኝ ከመንበሩ አንስታለች።
በ2023 በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ አራት ከግብፅ፣ ጊኒ እና ማላዊ ጋር ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያከናወነ ይገኛል። በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የዛሬ ሳምንት የተጫወተችው ግብፅ ከከፍተኛ ብልጫ ጋር ሁለት ለምንም ከተረታች በኋላ ምስቅልቅል ውስጥ የገባች ይመስላል። ከደቂቃዎች በፊት ይፋ በሆነው መረጃ መሰረት ደግሞ የሀገሪቱ የእግር ኳስ ማኅበር የብሔራዊ ቡድኑን አሠልጣኝ ኢሀብ ጋላል ከመንበሩ ማንሳቱን ይጠቁማል።
የ54 ዓመቱ አሠልጣኝ በቡድኑ ገና 2 ወር ያልሞላቸው ቢሆንም በኢትዮጵያ የደረሰባቸው ሽንፈት መንበራቸው እንዲንገጫገጭ አድርጓል። ይባስ ከትናንት በስትያ በወዳጅነት ጨዋታ በደቡብ ኮሪያ የደረሰባቸው የ4ለ1 ሽንፈት የእግር ኳስ ማኅበሩ ውሳኔ እንዲወስን እንዳደረገው ተመላክቷል።
በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ግብፅ በቀጣይ ከሀገር ውጪ ያለ አሠልጣኝ ልትሾም እንደምትችልም እየተዘገበ ይገኛል።