ጌታነህ ከበደ ቅጣቱ ተሽሮለታል

በ25ኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተደረገ ጨዋታ ቅጣት ተላልፎበት የነበረው የወልቂጤ ከተማው አምበል ወደ ሜዳ ይመለሳል።

ወልቂጤ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን የገጠመበት የ25ኛ ሳምንት ጨዋታ 1-1 ከተጠናቀቀ በኋላ ከተሰሙ የዲሲፕሊን ቅጣቶች መካከል የሰራተኞቹ አምበል የተጣለበት የሦስት ጨዋታ ቅጣት አንዱ ነበር።

ተጫዋቹ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በዳኞች ላይ ያልተገባ ዘለፋን ሰንዝሯል በሚል ነበር በጨዋታው ኮሚሽነር በቀረበበት ሪፖርት መነሻነት ነበር በሊጉ አክሲዮን ማህበር ለቅጣት የተዳረገው።

ሆኖም ተጫዋቹ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲስፕሊን ኮሚቴ ይገባኝ መጠየቁን ተከትሎ ኮሚቴው ውሳኔውን ተመልክቷል። በዚህም መሰረት ተጫዋቹ ተጠያቂ የተደረገበት ጉዳይ በዳኞች ሪፖርት ያልቀረበበት መሆኑን ፣ የተጫዋቹ ጥፋት የውድድር ሂደቱን አደጋ ላይ የማይጥል መሆኑን እና ክለቡ ተጫዋቹን በዚህ መልክ በማጣቱ በውጤት ደረጃ ጉዳት ላይ እንዳይወድቅ በማሰብ የሊግ ካምፓኒውን ውሳኔ ቀልብሶታል። በዚህም መሰረት ጌታነህ ከበደ ላይ የተላለፈው ቅጣት የተሻረ ሲሆን ኮሚቴው በቀጣይ ጨዋታዎች አጥቂው ክለቡን እንዲያገለግል ውሳኔ አሳልፏል።