በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች በዚህኛው ፅሁፋችን ተዳሰዋል።
👉 ስሜታዊ ሆኖ የታየው አቡበከር ናስር የከፍተኛ ጎል አግቢነት መሪነቱን ተቀላቅሏል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብፅ አቻውን በረታበት ጨዋታ ድንቅ ብቃቱን አሳይቶ የተመለሰው አቡበከር ናስር በክለቡ ከጉዳት ጋር በተያያዘ በመጨረሻዎቹ ጥቂት ጨዋታዎች አስቸጋሪ ጊዜያትን ቢያሳልፍም በአዳማው ጨዋታ ግን አቡበከር ናስር በሙሉ ጤንነት ሲገኝ ምን ማድረግ እንደሚችል ዳግም አሳይቷል።
አቡበከር ድንቅ ሆኖ ባረፈደበት ጨዋታ በተለይ ኃይልን ቀላቅለው ከሚጫወቱት ሁለቱ የአዳማ ከተማ የመሀል ተከላካዮች ከፍተኛ አካላዊ ጉሽሚያ ቢደርስበትም የጨዋታውን ሂደት በሚወስኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፎ ከማድረግ ያገደው አልነበረም። በተለይም ከሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ጀርባ አፈትልኮ በመሮጥ በተደጋጋሚ አደጋ ለመደቀን ጥረት ሲያደርግ አስተውለናል።
በጨዋታው ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው አቡበከር በተለይ በ79ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ግብ ፍፁም የተለየች ነበረች። በጨዋታው ሲያደርገው እንደነበረው ከጀርባ በመሮጥ ከአስራት ቱንጆ የደረሰውን ኳስ በአዳማ ሳጥን ውስጥ በመገኘት በቅድሚያ በሰውነቱ አዲስ ተስፋዬን አታሎ ኳሱን ወደ ቀኝ በመመለስ አስከትሎም በፍጥነት ኳሱን ሊያስጥል የመጣውን ቶማስ ስምረቱንም በማታለል ወደ ግብ የላካት እና ያስቆጠራት ኳስ እጅግ አስደናቂ ነበረች።
በእርግጥ ከሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ጋር በተያያዘ የወቅቱ የሀገሪቱ ምርጥ የሆነው ተጫዋቹ በጨዋታው ሁለት ቅፀበቶች ላይ ያሳየው ባህሪ በዕለቱ ያስመለከተውን ድንቅ ብቃትም ሆነ በጥቅሉ አሁን የሚገኝበትን ደረጃ የሚመጥን አልነበረም። በመጀመሪያ ቶማስ ስምረቱ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ ኢንተርናሽናል አርቢትር በላይ ታደሰ ክስተቱን በቢጫ ካርድ በማለፋቸው በመቀጠል ደግሞ አዲስ ተስፋዬ ጥፋት ሰርቶብኛል ብሎ ባመነበት ቅፅበት እጅግ የተጋነነ እስጥ አገባ ውስጥ ገብቶ ለቃላት ልውውጥ እና ለጉሽሚያ ሲጋበዝ ተመልክተነዋል። በተለይም የመጀመሪያውን አጋጣሚ አርቢትሩ በትዕግስት አለፉት እንጂ ሁለተኛው ክስተት ላይ የተመለከተው የቢጫ ካርድ ወደ ቀይነት የማደግ ዕድል ነበረው። ተጫዋቹ ከፊቱ ከሚጠብቀው በከፍተኛ ደረጃ የመጫወት ዕድል አንፃርም መሰል ስሜታዊነት ሊታይበት እንደማይገባ እና የግል ክህሎቱን በሚመጥን ብስለት ነገሮችን ማሳለፍ እንደሚገባው መጠቆም እንወዳለን።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በሊጉ አዲስ ክብረ ወሰንን በማስመዝገብ በ29 ግቦች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው አቡበከር ናስር ዘንድሮም ወደ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብር እየተንደረደረ ይገኛል።
11 ግቦች ላይ ሆኖ የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የአዳማ ከተማን ጨዋታ ያደረገው አቡበከር በጨዋታው ሁለት ተጨማሪ ግቦችን በማስቆጠር በሊጉ በአጠቃላይ ያስቆጠራቸውን የግብ መጠን ወደ 13 በማሳደግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ከይገዙ ቦጋለ እና ጌታነህ ከበደ ጋር በጣምራ እየመራ ይገኛል። ምንም እንኳን ከአቡበከር ናስር የማድረግ አቅም አንፃር 13 ግቦች እጅግ ደካማ ቁጥር ቢሆንም ወደ ደቡብ አፍሪካ ከማቅናቱ በፊት የመጨረሻው በሆነው የውድድር ዘመን ለተከታታይ ሁለት የውድድር ዘመናት በከፍተኛ አስቆጣሪነት ስለማጠናቀቅ ያልማል።
👉 ኦሴይ ማዉሊ ባህር ዳርን ይታደግ ይሆን ?
ጋናዊው አጥቂ ኦሴይ ማውሊ ባህር ዳር ከተማ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ነጥብ ሲጋራ እጅግ ድንቅ የሆነ ብቃትን በግሉ ማሳየት ችሏል።
እንደ ቡድን ከዕቅድ በታች እየተንቀሳቀሰ በሚገኘው የባህር ዳር ከተማ ስብስብ ውስጥ በግለሰብ ደረጃ ፍፁም ደካማ ጊዜ ካሳለፉ ተጫዋቾች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደበው ማውሊ እስከ 25ኛው የጨዋታ ሳምንት ድረስ ለቡድኑ 14 ጨዋታዎች አድርጎ በዚህም ሦስት ግቦችን ብቻ ማስቆጠር ችሏል።
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ትልቅ ትርጉም በነበረው እና ከሊጉ ጠንካራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጉት ወሳኝ ጨዋታ ግን እጅግ አስደናቂ ብቃቱን ማሳየት ችሏል። በጨዋታው ምንም እንኳን በፊት አጥቂነት ቢጀምርም በተለይም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ፊት እንዲሁም ከአማካዮቻቸው ጀርባ በሚገኘው የሜዳ ክፍል ላይ በነፃነት በመገኘት አደገኛ ሙከራዎችን ለማድረግ ሲጥር አስተውለናል። በእነዚህ ቦታዎች በመገኘት በቀጥታ ወደ ግብ የሚልካቸው ኳሶች እጅግ አደገኛ ነበሩ።
ከርቀት ካደረጋቸው ሙከራቸው ባለፈ በ29ኛው ደቂቃ ላይ በሜዳው የላይኛው ክፍል ከተነጠቀ ኳስ መነሻ ያዳረገችን አጋጣሚ ከሳጥን ውጪ በመምታት ያስቆጠረ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ግርማ ዲሳሳ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።
በጉዳት እና ቅጣት ቡድኑን በሚገባ ማገልገል ሳይችል የቆየው ኦሲ ማውሊ በሊጉ ጅማሮ ላይ ለባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ያሳየውን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ልክ እንደ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በቀጣይ በሚቀሩት ጥቂት ጨዋታዎች በመድገም ይክሳቸው ይሆን ? የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
👉 ወንድሜነህ ደረጀ ወደ ሜዳ ተመልሷል
በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ቡድኑን ከባህር ዳር ከተማ ከተቀላቀለ ወዲህ የኢትዮጵያ ቡና ተቀዳሚ የመሀል ተከላካይ አማራጭ የነበረው ወንድሜነህ ደረጀ በተለያዩ ምክንያቶች በተመራጭነት ዝርዝር ውስጥ ቦታው የወረደ ይመስላል።
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቡድኑ በተቀዳሚ የመሀል ተከላካይ አማራጭነት አበበ ጥላሁንን በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከገዛኸኝ ደሳለኝ እና በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ደግሞ ከቴዎድሮስ በቀለ ጋር በተደጋጋሚ ቢጠቀሙትም ወንድሜነህ ደረጀ ግን እምብዛም የመሰለፍ ዕድል ሲያገኝ አልተመለከትንም።
በዘንድሮ የውድድር ዘመን የዚህኛውን የጨዋታ ሳምንት ሳይጨምር በስድስት ጨዋታዎች በድምሩ ለ449 ደቂቃዎች ያህል የቡድኑን መለያ ለብሶ መጫወት የቻለው ወንድሜነህ ደረጀ ለመጨረሻ ጊዜ ለቡድኑ ተሰልፎ መጫወት የቻለው በ16ኛ የጨዋታ ሳምንት መጋቢት 22 ቡድኑ ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ ሲጋራ የነበረ ሲሆን ከ10 የጨዋታ ሳምንት በኋላ ዳግም ወደ ሜዳ ተመልሷል።
ወደ ጨዋታ በተመለሰበት የአዳማው ጨዋታ ወደ መሀል ሜዳ ተጠግቶ ለመከላከል ያሰበው ቡድን በጥቂት አጋጣሚዎች ከተከላካይ ጀርባ በመሮጥ ረገድ አደገኛ የነበሩትን የአዳማ አጥቂዎችን በመቆጣጠር ረገድ ግን ተቸግሮ ተስተውሏል።
ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሰው ወንድሜነህ ደረጀ በቀሪዎቹ ጨዋታዎች የመጀመሪያ ተመራጭነቱን ያስቀጥላል ወይ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
👉 ቃሉን የጠበቀው ኤሪክ ካፓይቶ
የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ በነበረው እና አርባምንጭ ከተማን ከሲዳማ ቡና ባገናኘው ጨዋታ ላይ ኬኒያዊው አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶ የጨዋታው ኮከብ ያሰኘውን ድንቅ ብቃት ማሳየት ችሏል።
ቡድኑ ሲዳማ ቡናን 2-1 በረታበት ጨዋታ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ኤሪክ ካፓይቶ በ32ኛው ደቂቃ ላይ እንዳልካቸው መስፍን የደረሰውን ተንጠልጣይ ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠረ ሲሆን በተጨማሪም በ42ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ያኩቡ መሀመድ ላይ ጫና በማሳደር በነጠቀው ኳስ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር ቡድኑን ባለድል አድርጓል።
በሊጉ በድምሩ አምስት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው አጥቂው ሦስቱን ከፍፁም ቅጣት ምት የተገኙ ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ መለያ ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ራሱን ሲያስተዋውቅ በፊት አጥቂነት ሚና የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን ተጫዋቹ ይበልጥ ከግራ መስመር እየተነሳ እንዲጫወት እየተገደደ ይገኛል። በመሆኑም የሲዳማው ጨዋታ ተጫዋቹ ከመስመር ይልቅ ይበልጥ በሳጥን ውስጥ እየተገኘ የመጫወት ነፃነት እያገኘ ሲጫወት የተሻለ መንቀሳቀስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቶ አልፏል።
በተጨማሪም ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እንደተናገረው በኬንያ ሊግ በሁለት አጋጣሚዎች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው ኤሪክ በሚገባ ቡድኑን እያገለገለ እንደማይገኝ እና ይህን ለማሻሻል በቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች የተሻለ ነገር እንደሚያደርግ ቃል መግባቱን የገለፁ ሲሆን እሱም ይህን ገና በመጀመሪያው ጨዋታ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።
👉 ራሱን በሊጉ በደንብ የሸጠው አላዛር ማርቆስ
በፕሪሚየር ሊጉ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሚገባ አቅማቸውን ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የጅማ አባ ጅፋሩ ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ ነው።
ምንም እንኳን እንደ ቡድን ጅማ አባ ጅፋር በሰንጠረዡ በ15ኛ ደረጃ ላይ በ23 ነጥብ ቢገኙም በግል ግን የተሻለ ጥረት እያደረጉ የሚገኙ ውስን ተጫዋቾች ይገኛሉ። በተለይም በቀላሉ ለተጋጣሚዎቹ ዕድል ከሚፈቅደው የቡድኑ የመከላከል መዋቅር በስተጀርባ ያለው አላዛር በየጨዋታው በርከት ያሉ ሙከራዎችን ሲያመክን ማስተዋል ይቻላል።
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው በወጡበት ጨዋታ ወጣቱ ግብ ጠባቂ ቡድኑን በጨዋታ ያቆዩ በርከት ያሉ አጋጣሚዎችን ሲያመክን የተመለከትን ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽም በአየር ላይ ኳሶች ላይ የነበረው ንቃት እና ቅልጥፍና የሚደነቅ ነበር።
ከዚህም በላይ የተሻለ ግብ ጠባቂ የመሆን አቅም ያለው አላዛር ቡድኑ ወደ ከፍተኛ ሊግ ቢወርድ እንኳን በሊጉ የሚገኙ ክለቦች ለግልጋሎቱ እንዲጫረቱ የሚያስገድድ ሆኗል።
👉 ሁለቱን ወንድማማቾች ያገናኘው ጨዋታ
ወንድማማቾች በተቃራኒ ሲጋጠሙ የመመልከት ነገር በእግርኳሳችን አሁን አሁን ይበልጥ እየተመለደ መጥቷል።
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ተረኞቹ “የመስፍን ቤተሰቦች” ሆነዋል። አርባምንጭ ከተማ ከሲዳማ ከተማ ጋር ባደረጉት የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ ሙሉዓለም መስፍን በሲዳማ ቡና በኩል እንዲሁም እንዳልካቸው መስፍን ደግሞ በአርባምንጭ ከተማዎች በኩል ተሰልፈው ጨዋታቸውን አድርገዋል።
በጨዋታው የመጨረሻው ሳቅ የታናሽ ማለትም የእንዳልካቸው መስፍን ስትሆን በጨዋታውም ኤሪክ ካፖይቶ ያስቆጠራት የመጀመሪያዋ ግብ ከእንዳልካቸውመስፍን እግር የተነሳች ነበር።
👉 ኦሮ-አጎሮ ለመመለስ እየተንደረደ ነው
ጉዳት ላይ የከረመው የፈረሰኞቹ የፊት አውራሪ ወደ ሜዳ ለመመለስ ከጫፍ ደርሷል።
ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ወደ ሜዳ ያልተመለሰው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ሊጉ ከዕረፍት ሲመለስ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ተጫዋቹ ጨዋታውን በተጠባባቂ ወንበር ሆኖ ተከታትሏል።
10 ግቦችን በማስቆጠር ከሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝርን ረዘም ላሉ ጊዜያት ሲመራ የቆየው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ በቀጣዮቹ ጥቂት ጨዋታዎች በፍጥነት ወደ ጨዋታ ዝግጁነት ለመመለስ እየጣረ ሲሆን ቡድኑን በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይም ወደ ዋንጫ በሚያደርገው ፉክክር ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።