ሪፖርት | ፈረሰኞቹ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁለቱ አጋማሾች ባስቆጠሯቸው ግቦች ወልቂጤ ከተማን በመርታት ከተከታታይ ነጥብ መጣሎች በኋላ ይበልጥ ወደ ዋንጫው የሚያስጠጋቸውን ድል አሳክተዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም አማካይ ስፍራ ላይ ላይ የዓብስራ ተስፋዬ እና ሀይደር ሸረፋን አስወጥተው በምትካቸው በረከት ወልዴ እና ከነዓን ማርክነህን ተክተው አስገብተዋል።

በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ ከመከላከያ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ውስጥ ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች ረመዳን የሱፍ ፣ ተስፋዬ ነጋሽ እና በኃይሉ ተሻገርን ወደ ተጠባባቂ ወንበር አውርደው በምትካቸው ዮናታን ፍሰሃ ፣ ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ እና አቡበከር ሳኒን የመጀመሪያ ተመራጭ በማድረግ ጀምረዋል።

ገና ከጅምሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከፍ ባለ የማጥቃት ፍላጎት በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ ባልተለመደ መልኩ በጥንቃቄ ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ በተመለከትንበት ጨዋታ ፈረሰኞቹ ፍፁም የሆነ የበላይነት የነበራቸው ቢሆንም በማጥቃት ሲሶ የነበራቸው አፈፃፀም ግን የነበራቸውን የበላይነት የሚያሳይ አልነበረም።

በጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ቀኝ ባደላ የማጥቃት ሂደት ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ፤ በዚህም ሂደት ጥቂት የማይባሉ ግማሽ ዕድሎችን ቢፈጥሩም በደካማ ውሳኔ አሳጣጥ ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለያየ ምክንያት የሳሳ ስብስብን ይዘው የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች ገና በ17ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ቅያሬ በአስገዳጅ ሁኔታ ለማድረግ ተገደዋል ፤ አማካዩ ኤዲ ኤሞሞ ንጎይ ባስተናገደው ጉዳት መነሻነት በበኃይሉ ተሻገር ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራ በ20ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬምፖንግ ሜንሱ በቀኝ የሳጥን ጠርዝ አካባቢ ያገኙትን የቅጣት ምት አጋጣሚ ጋናዊው ተከላካይ በግሩም ሁኔታ የላካት እና ሰዒድ ሀብታሙ በግሩም ቅልጥፍና ባዳነበት ኳስ የተመለከትን ሲሆን በ25ኛው ደቂቃ ግን የሚገባቸውን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ሄኖክ አዱኛ ያሻማውን የማዕዘን ምት አማኑኤል ገ/ሚካኤል በነፃነት በግንባሩ ገጭቶ የሞከራት ኳስ በግቡ አግዳሚ ስትመለስ የወልቂጤው ግብ ጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙ የተመለሰችውን ኳስ ለመቆጣጠር ባደረገው ጥረት ከዮናስ በርታ ጋር ባለመናበባቸው ምክንያት የተፈጠረውን ዕድል ከነዓን ማርክነህ ተጠቅሞ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

በጨዋታው አብዱልከሪም ወርቁን በሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥርነት ለመጠቀም ጥረት ያደረጉት ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ራሳቸው ሜዳ ተገፍተው ካሳለፉባቸው ደቂቃዎች ውጪ እጅግ ውስን በሆኑ አጋጣሚዎች የመልሶ ማጥቃት ለመሰንዘር የሚያስችሉ ዕድሎችን ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በአጋማሹ ያደረጉት ብቸኛ ሙከራም በ37ኛው ደቂቃ ነበር ፤ በጥሩ የቅብብል ሂደት በኃይሉ ተሻገር ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ጫላ ተሺታ በግሩም ሁኔታ በግራ እግሩ ያደረጋት እና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት አጋጣሚ ብቻ ነበረች።

ሌላኛው በአጋማሹ ትኩር የሳበው አጋጣሚ በቅርቡ ከጉዳት የተመለሰው አቤል ያለው በአንድ አጋጣሚ በሁለት የወልቂጤ ተጫዋቾች መካከል ለማለፍ ባደረገው ጥረት ወቅት ባስተናገደው ጉዳት መነሻነት በ38ኛው ደቂቃ በግዳጅ በዳግማዊ ዓርአያ ተቀይሮ ከሜዳ የመውጣቱ ነገር ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በመጀመሪያው አጋማሽ ለዝርግ የኃላ አራት ተከላካይ የቀረበ የነበረውን የቡድኑ የተከላካይ ተጫዋቾች ምርጫን ሆነ አጠቃላይ የማጥቃት ሂደቱን በተወሰነ መልኩ ማስተካከል የፈለጉት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ዮናስ በርታ እና ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስን አስወጥተው በምትካቸው አላዛር ዘወዱ እና ረመዳን የሱፍን አስገብተዋል። ከለውጦቹ በኋላ ወልቂጤዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም በተለየ መልኩ እንደ ቡድን በማጥቃት ረገድ በተለይ በሁለቱ የመስመር ተከላካዮች የተደገፉ ኳስን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሙከራ ሲያደርጉ አስተውለናል።

በአንፃሩ በአጋማሹ በመጠኑ የተቀዛቀዙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ግን ሳይጠበቅ ሁለተኛ ግባቸውን ለማግኘት ቀርበው ነበር ፤ 53ኛው ደቂቃ ላይ ጋቶች ፖኖም ያደረሰውን ድንቅ ኳስ ከነዓን ማርክነህ ከግራ ወደ ውስጥ ያሳለፈውን እየተንደረደረ የመጣው በረከት ወልዴ ተረጋግቶ አስቆጠራት ሲባል ከግቡ አናት በላይ የሰደዳት ኳስ ፍፁም አስቆጭ ነበረች።

ጨዋታውን በመሩት አልቢትር ኃየለየሱስ ባዘዘው ተደጋጋሚ ፊሽካዎች እየተቆራረጠ በቀጠለው ጨዋታ ወልቂጤ ከተማዎች ይበልጥ በጀብደኝነት ማጥቃታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በዚህም በተለይ ተቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ረመዳን የሱፍ እና አላዛር ዘውዱ ወሳኝ ሚና ሲወጡ አስተውለናል።

በ77ኛው ደቂቃ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከማዕዘን ምት ያሻሙትን ኳስ ሰዒድ ሀብታሙ በአግባቡ መቆጣጠር አለመቻሉን ተክሎ በተፈጠረ ዕድል ከነዓን ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በወልቂጤ ተጫዋቾች ርብርብ የዳነች ሲሆን በአንድ ደቂቃ ልዩነት ግን ፈረሰኞቹ አሸናፊነታቸውን ያረጋገጠችን ግብ አግኝተዋል። ጫላ ተሺታ ዳግማዊ አርዓያ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት ጋቶች ፖኖም አስቆጥሮ ቅዱስ ጊዮርጊሶች 2-0 እንዲመሩ አስችሏል።

በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተደጋጋሚ የተጫዋቾች ለውጦችን በማድረግ ጨዋታውን ተቆጣጥረው የወጡ ሲሆን ፤ በ89ኛው ደቂቃ ላይም ረዘም ላሉ ጊዜያት ከሜዳ ርቆ የሰነበተው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ከነዓን ማርክነህን ተክቶ በመግባት ወደ ሜዳ የተመለሰባቸውን ጥቂት የጨዋታ ደቂቃዎችን ያሳለፈ ሲሆን አንድ ግሩም የግብ አጋጣሚን እንዲሁ መፍጠር ችሏል።