የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 ወልቂጤ ከተማ

የዛሬ ረፋዱ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

“በጣም ጥሩ ነው ጨዋታው። ኳስ ይዘን ፣ ኳስ ተጫውተን በብዙ ሙከራዎች ወደ ግብ ቀርበን ነበር። ሁለት ጎሎች አግብተን ጥሩ ውጤት ይዘን ወጥተናል።

በአጋማሾቹ መካከል ስለነበረው ልዩነት

” ምንም ልዩነት የለውም። ወልቂጤም ጎል ስለሚፈልግ ሊመጣ ይችላል። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ እኛ ተረጋግተን ማድረግ ያለብንን አድርገን ሁለተኛውም አጋማሽ ላይ ጎል አግብተን ውጤቱን በትክክል ይዘን ወጥተናል።

ስለከነዓን ማርክነህ ቀዳሚ ተሰላፊነት ውሳኔ

“አዎ ! በትክክል ውሳኔዬ ትክክል ነው። ማንኛቸውም ተጫዋቾች ያላቸውን አቅም በትክክል እና በሰዓቱ ይሰጣሉ። ቤንችም ያሉት የተሰለፉትም ጥሩ አቅም አላቸው። ይሄን ስለማምን እና የተሻለ ነገር ስለነበረው ያለፈው ጨዋታ ላይም ጎል አግብቶ ስለነበር ምርጥ 11 ውስጥ አስገብቼዋለው። አዎ ጥሩ ነገር ሰጥቶኛል ፤ ነገም ጥሩ ነገር መስራት ይችላል።

ስለዋንጫው ፉክክር

“ስለዋንጫው ማሰብ አልፈልግም። ከፊታችን አሁንም ጠንካራ ጨዋታ አለን። ለእኛ ሁሉም ጨዋታዎች ጠንካሮች ናቸው። ለዛ ጨዋታ ያሉንን ጊዜዎች እና ቀኖችን አጣበን የተሻለ ነገር ለመስራት ነው የምንሄደው።”

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

” በመጀመሪያው አጋማሽ አስበነው የነበረው ነገር በተጎዳብን ተጫዋች ተበላሽቶብናል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን በተወሰነ መልኩ ራሳችንን አስተካክለን ወደ ጨዋታው ተመልሰናል። ነገር ግን ፍፁም ቅጣት ምቱ የጨዋታውን መንፈስ ቀይሮታል።

የመስመር ተመላላሾች ቆመው መከላከላቸው ዋጋ ስለማስከፈሉ

“አዎ ! ወደ ኋላ እንድናፈገፍግ አድርጎናል። በእርግጥ እኔ አስቤ የነበረው እንደዛ አልነበረም። ነገር ግን አስገዳጅ ሆኖብን ይመስለኛል ልጆቻችን ወደ ኋላ አፈግፍገዋል። ያንን እንዲለውጡት ነው ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተነጋገርነው። በተወሰነ መልኩ ለውጠነው ገብተናል።

ያለንፁህ ዘጠኝ ቁጥር ጨዋታውን መጀመራቸው ስለነበረው ተፅዕኖ

” አዎ ይኖረዋል ! ምክንያቱም ከተለመደው አጨዋወት ወደ ሌላ አጨዋወት ስትገባ ያንን አጨዋወት እስክትላመድ ትቸገራለህ ፤ ያንን ነው የተመለከትነው። ተፈጥሯዊ አጥቂ አልተጠቀምንም። ምንአልባት አላዛር ተቀይሮ ከገባ በኋላ ነው ያንን ምልክት ያየነው። ዞሮ ዝሮ ተፈጥሯዊ አጥቂ አለመኖሩ ጎድቶናል ብዬ አስባለሁ።

ስለማውረድ ስጋት

“ምንም አያሰጋንም። ምክንያቱም ቀሪ ዘጠኝ ነጥቦች አሉ። የምናሳካቸው ጨዋታዎች ይኖራሉ ብዬ አምናለሁ ፤ ምንም አያስፈራኝም።”