የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች ልምምድ አቁመዋል

ነገ ሲዳማ ቡናን የሚገጥሙት የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች ትናንት እና ዛሬ ልምምድ እንዳልሰሩ ታውቋል።

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሜዳ ላይ ፍልሚያዎች በደረጃ ሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ አጓጊ ፉክክር እያስመለከቱ ባለበት በአሁኑ ሰዓት አንዳንድ ክለቦች ከሜዳ ውጪ በሚፈጠሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሊጉን ውበቱ እያጠለሹ ይገኛሉ። ከሰሞኑን የወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች ሦስት ቀን ብቻ የሰበታ ከተማ ተጫዋቾች ደግሞ ከ6 ባልበለጡ ተጫዋቾች ሲዘጋጁ የነበረ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋቾች በበኩላቸው 5 ቀናትን ልምምድ ሳይሰሩ የ26ኛ ሳምንት መርሐ-ግብራቸውን እንዳከናወኑ መገለፁ ይታወሳል። አሁን በደረሰን መረጃ ደግሞ የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች በተመሳሳይ ከደሞዝ ጋር በተገናኘ ትናንት እና ዛሬ ልምምድ አልሰሩም።

ነገ 10 ሰዓት ከሲዳማ ቡና ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያለው ክለቡ ትናንት ከ9:00 ጀምሮ ለአንድ ሰዓት የሚዘልቅ ልምምድ ለማድረግ ቀጠሮ የነበረው ቢሆንም ከምሳ በኋላ ተጫዋቾቹ ተሰባስበው ተስማምተው የልምምድ መርሐ-ግብሩ ሳይከናወን ቀርቷል። ክለቡ ዛሬ ረፋድ ከ3 እስከ 4 ሰዓት ሌላ ልምምድ ቢኖረውም ተጫዋቾች ከጋራ ይልቅ በተናጥል ብቻ በያሉበት መንቀሳቀስን መርጠው ልምምዱ አልተሰራል። ከተጫዋቾች ባገኘነው መረጃ መሰረት ዓምና በክለቡ የነበሩት የ3 ዘንድሮ የተቀላቀሉት ደግሞ የ2 ወር ደሞዝ ስላልተፈፀመላቸው ልምምድ አልሰሩም።

ተጫዋቾቹ የጋራ ልምምዶችን ባያደርጉም የነገውን ጨዋታ እንደሚከውኑ ተጠቅሷል። ለዚህም የኮቪድ-19 ክትባት የሌላቸው ተጫዋቾች ረፋድ ላይ ምርመራ እንዳከናወኑ አውቀናል። ክለቡም የተጫዋቾቹን ጥያቄ ለመመለስ እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ የሰማን ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት ደሞዛቸው እንዲደርሳቸው ለማድረግ እየተጣረ እንደሆነ ተነግሮናል።