ሀዋሳ ከተማ በኤፍሬም አሻሞ እና ብሩክ በየነ ጎሎች ታግዞ ባህር ዳር ከተማን በመርታት ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።
ድሬዳዋ ከተማን 3ለ1 አሸንፈው የመጡት ሀዋሳ ከተማዎች አንድም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ የተጋሩት ባህር ዳር ከተማዎች በበኩላቸው መሳይ አገኘሁን ብቻ በግርማ ዲሳሳ ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል።
በጥሩ ፉክክር የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና ሦስት ደቂቃ ሳይሞላው መሪ ሊያገኝ ነበር። በዚህ ደቂቃም የባህር ዳሩ የመስመር አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን በግራ እግሩ የጨዋታውን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሰንዝሮ ቁመታሙ የግብ ዘብ መሐመድ ሙንታሪ አምክኖበታል። ይሁ አጥቂ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ሌላ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ፈጥቶ በድጋሜ ግብ ጠባቂው አድኖበታል። ሁለት ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራዎች የተሰነዘረባቸው ሀዋሳዎች የኳስ ቁጥጥር ላይ ፍላጎት ሳያሳዩ የመልሶ ማጥቃቶች ላይ የተንጠለጠለ አጨዋወት መከተል ይዘዋል። ሩብ ሰዓት ሊደርስ ሲልም ወንድማገኝ ኃይሉ ለብሩክ በየነ ባሻማው ኳስ ጥሩ ዕድል ፈጥረው ተመልሰዋል።
በጥሩ ተነሳሽነት ሲጫወቱ የታዩት ባህር ዳሮች በ17ኛው ደቂቃ ካልተጠበቀ ምንጭ ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ተከላካዩ መናፍ ዐወል ከመሐል ሜዳ በቀጥታ ወደ ግብ የመታውን ኳስ መሐመድ ሙንታሪ ከግቡ አግዳሚ ጋር ተጋግዞ መስመሩን እንዳያልፍ አድርጓል። ከሳጥን ሳጥን ጥሩ ምልልስ በማሳየት ለዐይን ሳቢ የሆነው ጨዋታ የመናፍ ሙከራ ከተደረገ ከሰከንዶች በኋላ በብሩክ አማካኝነት የተደረገን የግንባር ጥቃት አስመልክቷል።
ጨዋታው 38ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቀዝቀዝ ብለው የጀመሩት ሀይቆቹ መሪ ሆነውበታል። በዚህም ካሉጂ ሙንዲያ ከራሱ ሜዳ በረጅሙ የላከውን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ የግብ ክልሉን ለቆ የወጣው ፋሲል ገብረሚካኤልን ስህተት ተከትሎ ያገኘውን ኳስ ከመረብ ጋር አዋህዶታል። ኤፍሬም አጋማሹ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ላይም ከሳጥን ውጪ ጥሩ ኳስ ሞክሮ ነበር።
ሁለተኛው አጋማሽ ገና በተጀመረ በ90ኛው ሰከንድ ሀዋሳ መሪነቱን ወደ ሁለት አሳድጓል። በግራ የሳጥኑ ክፍል የወንድማገኝ ኃይሉ እና ብሩክ በየነ ቅብብሎች በተዘናጉት የባህር ዳር ተከላካዮች ተገቢው ሽፋን ሳይሰጣቸው ቀርቶ ብሩክ ኳሱን ወደ ቀኝ በማመቻቸት በድንቅ ሁኔታ ወደ ግብ ሲልከው ፋሲል ገብረሚካኤልን በማለፍ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ጎል ሆኗል።
ጨዋታው እየከበደባቸው የሄደው ባህር ዳሮች ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ዓሊ ለማውሊ አመቻችቶለት ግዙፉ አጥቂ በግራ እግሩ በሞከረው ኳስ ወደ ጨዋታው ሊመለሱ ነበር። የቡድኑ አሠልጣኝ አብርሃምም ሁለተኛው ጎል ከተቆጠረ በኋላ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በማስገባት ከባዱን ፈተና ለመጋፈጥ ጥረዋል። በተለይ ፍፁም በ60ዎቹ ደቂቃዎች ለማውሊ እና ተመስገን የላካቸው ኳሶች ዋጋቸው ከፍ ያለ ነበር። በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ቡድኑ በላይኛው ሜዳ በመሆን ቢንቀሳቀስም ጠጣሩን የሀዋሳ የመከላከል መስመር ማለፍ አቅቶታል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተቀይሮ የገባው አደም ጥሩ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቢቀርም በጭማሪው ደቂቃ ኦሴ ማውሊ የማስተዛዘኛ ጎል እንዲያገኝ አመቻችቶ አቀብሏል። ጨዋታውም 2ለ1 ተጠናቋል።
በውጤቱ መሰረት ከ12 ጨዋታዎች በኋላ ተከታታይ ድላቸውን ያስመዘገቡት ሀዋሳዎች ነጥባቸውን 42 በማድረስ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል። ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ባህር ዳሮች ደግሞ በ30 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።