ወልቂጤ ከተማ ቡድን መሪውን አሰናብቷል

ጌታነህ ከበደ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የተነሳው ውዝግብ ቀጥሎ ክለቡ የቡድን መሪው ላይ የስንብት እርምጃ ወስዷል።

ከትላንት በስቲያ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ይግባኝ ሰሚ ኮሜቴ ከቀናት በፊት የተላፈበት ውሳኔ ተሽሮለት የነበረው ጌታነህ ከበደ ትላንት አመሻሽ ላይ በሊግ አክሲዮን ማህበሩ ውሳኔው ዳግም እንዲፀና የመደረጉ ጉዳይ ወልቂጤ ከተማዎች ያስቆጣ ነበር።

በዚህም ክለቡ ትላንት አመሻሽ ባወጣው መግለጫ የአክሲዮን ማህበሩን ውሳኔ ስለመቃወሙ መዘገባችን ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ዛሬ ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥም ‘ጌታነህ ከበደን ይጠቀማል ወይንስ አይጠቀምበትም ?’ የሚለው ጉዳይ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን በዚህም ጌታነህ ከበደን ሳይዝ የገባው ቡድን 2-0 በሆነ ውጤት ሽንፈት አስተናግዷል።

ውጤቱን ተከትሎ ከክለቡ ፅ/ቤት በኩል ወጪ በተደረገ ደብዳቤ ክለቡ የቡድን መሪውን አቶ ዐወል ከድርን ከኃላፊነታቸው የተነሱ መሆናቸው እና በእጃቸው የሚገኙ ንብረቶችን በሙሉ አስረክበው በመጪው ሰኞ በክለቡ ጽ/ቤት ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ስለመታዘዛቸው ያሳያል።

እርግጥ በደብዳቤው ላይ ከኃላፊነታቸው ስለመነሳታቸው በግልፅ የቀረበ ምክንያት ባይኖርም በክለቡ ቦርድ ዘንድ ትላንት ምሽት በወጣው ደብዳቤ በግልፅ እንዳሳወቁት በዛሬው ጨዋታ ለጌታነህ ከበደ በፌደሬሽኑ የተወሰነው ውሳኔ እንዲፀና እና የተጫዋቹን ግልጋሎት እንዲሰጥ ፍላጎት የነበረ ሲሆን በክለቡ ሰዎች ዘንድ ይህን ውሳኔ የማስፈፀም ግዴታ የነበረባቸው የክለቡ ቡድን መሪ ቢሆኑም ይህን ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻላቸው ውሳኔው መተላለፉን ለማወቅ ችለናል። በቀጣይ ሰኞ ክለቡ ከአሰልጣኝ ቡድኑ አባላት ጋርም በተመሳሳይ በጉዳዩ ዙርያ ስብሰባ ተቀምጦ የነበረውን ሁኔታ እንዲሁ እንደሚገመግም ለማወቅ ችሏል።

ከወልቂጤ ከተማ ውሳኔ ጋር ተያይዞ አቶ ዐወል ያላቸውን ሀሳብ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው ጌታነህ በቡድኑ ውስጥ እንዲካተት ትዕዛዝ የተላለፈላቸው በቃል ብቻ በመሆኑ ከሊጉ አክሲዮን ማህበር ግሳፄ ለመትረፍ እንዲሁም ይሰለፍ የሚል የፅሁፍ ማረጋገጫ ከክለቡ ስላልተሰጣቸውም ጭምር ተጫዋቹን በዕለቱ የቡድን ዝርዝር ውስጥ ሳያካትቱት መቅረታቸውን ነግረውናል።